የአብርሆት የመጻሕፍት ማሰባሰቢያ የመጀመሪያው ምዕራፍ የማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአንድ ወር ሲካሄድ የቆየው ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት የመጻሕፍት ማሰባሰቢያ የመጀመሪያው ምዕራፍ የማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የአዲስ አባበ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዮናስ ዘውዴ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡
ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ መጻሕፍ መስጠትን ባህል አድርጎ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
መጻሕፍት የማሰባሰቡ መርሐ ግብር በቀጣይ በሌላ ምዕራፍ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል፡፡
ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት÷ “ሚሊየን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ቃል ለአንድ ወር የሚቆይ የመጻሕፍት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በይፋ መጀመሩ ይታወቃል፡፡
መርሀ ግብሩ ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 29 የቆየ ሲሆን÷ 4 ሚሊየን መጻሕፍት የመያዝ አቅም ላለው ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ለማሟላት ያለመ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትን በማቋቋም ከ75 ዓመት በላይ የቆየ ልምድ ቢኖራትም ይህንኑ ልምድ ማስቀጠል ሳይቻል መቅረቱ በመርሀ ግብሩ ወቅት ተመላክቷል፡፡
ከአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ግንባታ መጠናቀቅ በኋላ በየግለሰቦች እጅ ላይ የሚገኙ ህትመታቸው የቆሙ እና ገበያ ላይ የማይገኙ መጻሕፍትን ከማህበረሰቡ ሲሰበሰብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
በሐብታሙ ተ/ስላሴ
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!