1443ኛው የኢድ አል አድሀ ዐረፋ በዓል በድሬዳዋ በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ተከበረ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 1443ኛው የኢድ አል አድሀ ዐረፋ በዓል በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በበዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ተከብሯል፡፡
በድሬዳዋ አየር መንገድ አካባቢ በሚገኘው የኢድ መስገጃ ሜዳ የተከበረው የአረፋ በአል ላይ በብዙ ሺህ የሚገመቱ የገጠርና የከተማ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተሳትፈዋል፡፡
በበአሉ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ወርሰሜ እና የካቢኔ አባላት፣ የየመስጅዱ ኢማሞች፣ ኡላማዎች እና ሼኾች ተሳታፊ ሆነዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ወርሰሜ ለመላው የአገሪቱ የሙስሊም ማህበረሰብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈው÷ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለአገር ሰላም ፣ ልማት እና ዕድገት እያበረከተ የሚገኘው ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል።
ይህን ተሳትፎ ይበልጥ በማሳደግ የፀረ ሰላም እና የፀረ ልማት አካላትን እና ሽብርተኞችን በመከላከል የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በስኬት እንዲጠናቀቅ ርብርባቸውን እንዲያጠናክሩ መጠየቃቸውን ነው ኢዜአ የዘገበው።
ይህ እለት ነቢዩ ሙሃመድ ዘረኝነትንና ጎጠኝነትን ያወገዙትበት በመሆኑ ሙስሊሞች ከመሰል አፍራሽ ተግባሮች ሊከለከሉ ይገባል- በጅማ ከተማ የፈትህ መስጂድ ኢማም ሼህ ሙሃመድ አሚን ተማም።
በጅማ ከተማ 1443ኛው የኢድ-አል-አድሃ አል እየተከበረ ነው።
በጅማ ከተማ የፈትህ መስጂድ ኢማም ሼህ ሙሃመድ አሚን ተማም፥ ሁሉም ሰው ፈጣሪውን ሊፈራና ከመጥፎ ነገሮች ልከለከልና እውቀትና ጉልበቱን ለመልካም ተግባር ልያውል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ይህ እለት የአላህ መልዕክተኛ ነቢዩ ሙሃመድ ዘረኝነትንና ጎጠኝነትን ያወገዙትበት በመሆኑ ሙስሊሞች አፍራሽ ከሆኑ መሰል ተግባሮች ሊከለከሉ ይገባል ብለዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ በአሉን ስያከብር የተቸገሩትን፣ የታመሙትንና አቅመ ደካሞችን ማሰብ እንዳለበት ሸህ መሃመድ አሚን ገልጸዋል።
የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ነጂብ ራያ፥ ህዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን በማጠናከር ሃገሩንና እምነቱን ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል።
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!