የፒኬኬ ታጣቂዎች የጦር መሳሪያቸውን አቃጠሉ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) የሰላም አማራጭ መቀበሉን ተከትሎ የቡድኑ ተዋጊዎች የጦር መሳሪያቸውን በይፋ አቃጥለዋል፡፡
ፒኬኬ ከአራት አስርት አመታት የትጥቅ ትግል በኋላ ከቱርክ መንግስት የቀረበውን የሰላም አማራጭ ጥሪ በመቀበል የትጥቅ ትግሉን በይፋ ማቁሙ ይታወሳል፡፡
ቡድኑ ውሳኔውን ያስተላለፈው ከፈረንጆቹ ግንቦት 5 እስከ 7 ባደረገው ኮንግረስ ሲሆን በቱርክ እስር ቤት የሚገኙትን የቡድኑ መሪ አብደላ ኦቻላን ቡድኑ የሰላማዊ አማራጭን እንዲቀበል ትዕዛዝ መስጠታቸው ተከትሎ ነው ወደ ስምምነት የመጣው፡፡
በዛሬው እለትም በርካታ የፒኬኬ ታጣቂዎች በአደባባይ የጦር መሳሪያቸውን በእሳት በማቃጠል በይፋ የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ማቆማቸውን አሳይተዋል፡፡
ቡድኑ ትጥቁን ያቃጠለው ከቱርክ መንግስት ጋር በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት ሲሆን፤ በሁለተኛው ዙር የትጥቅ ማስፈታት ሂደት ከቀናት በኋላ ተጨማሪ ትጥቆችን እንደሚያስወግድ ተመላክቷል፡፡
ፒኬኬ የኩርዲስታን ብሔርተኝነትን በማንገብ ኩርድን ነፃ ሀገር ለማድረግ አልሞ ላለፉት 40 ዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
በሚኪያስ አየለ