የክልሉ መንግስት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን ይወጣል -አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልሉ መንግስት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን ይወጣል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ተናገሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በጎግ ወረዳ ፑቻላ ቀበሌ እየተከናወነ ያለውን የቆላ ስንዴ ልማት የጎበኙ ሲሆን÷ በዚህ ወቅት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የስንዴ ምርት ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷ የክልሉ መንግስት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን ይወጣል ብለዋል፡፡
በክልሉ የስንዴ ምርት ለማምረት በ20 ሄክታር መሬት ላይ የቆላ ስንዴ የሙከራ እንቅስቃሴ መደረጉን እና እንቅስቃሴው አበረታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአቦቦና በጎግ ወረዳ 50 ሄክታር መሬት ለቆላ ስንዴ መዘጋጀቱን ጠቅሰው÷ በቀጣይ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች 1 ሺህ ሄክታር ለማልማት ታቅዷል ነው ያሉት፡፡
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ በበኩላቸው÷ በዘንድሮው በጀት ዓመት ለማልማት ከታቀደው 1 ሺህ ሄክታር የስንዴ ማሳ 500 ሄክታሩ በምዕራፍ ሁለት የግብርና እድገት ፕሮግራም የሚለማ እንደሆነ ገልፀዋል።
የቆላ ስንዴን ለማልማት የሚመለከታቸው አካላት በዘርፉ ተሰማርተው ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።