የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የሱዳን ጠቅላላ የደህንነት አገልግሎት በጋራ ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተመራ ልዑክ ከሱዳን ጠቅላላ የደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አህመድ ኢብራሂም አሊ ሙፍዲል እና ሌሎች ከፍተኛ የተቋሙ አመራሮች ጋር በመረጃና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በካርቱም መክሯል።
በውይይታቸው ሁለቱ ተቋማት ግንኙነታቸውን አጠናክረው በጋራ መስራታቸው ለሀገራቱ እና ለህዝቦች ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ በሚኖረው አስተዋፆ ዙሪያም መክረዋል።
ከውይይቱም በኋላም ሁለቱ ተቋማት የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መረጃ ለመለዋወጥ እና በጋራ ለመስራት የሚስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የስምምነቱ ትኩረትም ተቋማቱ በጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተሞክሮ እና መረጃ ለመለዋወጥ፣ የቀጠናው የጋራ ስጋት የሆነውን ሽብርተኝነት በጋራ መዋጋት ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል፣ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች በሰላም የመኖርና የመንቀሳቀስ ደህንነትን ማረጋገጥ እና የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ሰላም የሚጎዱ አካላትን በጋራ መከላከል ላይ በትብብር ለመስራት ያለመ ነው።
ልዑኩ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱል ፈታ አልቡራህንና ከሉዓላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር ሞሐመድ አምዳን ዳጋሎ ጋር በሀገራቱ ሰላምና ደኀንነት ዙሪያ መወያዩቱን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመላክቷል።