Fana: At a Speed of Life!

በገጠር አካባቢዎች የሶላር ኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽነትን ለማጠናከር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአርሶ አደሮችን የሶላር ኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው አለ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር፡፡

በሚኒስቴሩ የዩኤንዲፒ አፍሪካ ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ይመስላል ተፈራ እንዳሉት ÷ በኢትዮጵያ በርካታ የገጠር አካባቢዎች ላይ ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽነት ዝቅተኛ ነው፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም ከዋናው መስመር ርቀው የሚገኙ የገጠር አካባቢዎችን በሶላር ኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት መደረጉን አመልክተዋል፡፡

በዚህም መሰረት የዩኤንዲፒ አፍሪካ ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት በገጠር አካባቢዎች ሶላር ሚኒግሪዶችን በመትከል የሃይል ተዳራሽነት ለማስፋት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና ትግራይ ክልሎች የሚተገበር ሲሆን÷ ውጤታማነቱ ታይቶ በሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡

በገጠር አካባቢዎች ኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው÷ ለዚህም በዘርፉ የባለድርሻ አካላት ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት የሚኒ ግሪድ ፕሮጀክቶች በመንግሥት ብቻ ይተገበሩ ነበር ያሉት አስተባባሪው÷ አፍሪካ ሚኒግሪድ ፕሮጀክት ግን የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

በሶላር ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ስለሆነም ባለሃብቶች በዘርፉ በመሰማራት በርካታ ሕዝብ የሚኖርበትን የገጠር አካባቢ የሶላር ኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ባንኮችን ጨምሮ የፋይናንስ ተቋማት በሶላር ሃይል ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የብድር አቅርቦትን በማመቻቸት የበኩላቸውን ሚና እንዳጡም ጠይቀዋል፡፡

የፕሮጀክቱን ውጤታማነት በማጠናከር የሃይል ተደራሽነትን ለማስፋፋትና በሚኒ ግሪድ ልማት ላይ የሚታዩ ዋና ዋና ተግዳሮቶችን ለመፍታት የባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ታዳሽ ኃይልን መጠቀም የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን ከማሳደግ ባለፈ የገጠር አካባቢዎችን የሃይል ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.