ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተልዕኮውን እንዲያሳካ የሚሲዮን መሪዎች አይነተኛ ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተሰጠውን ተልዕኮ እንዲያሳካ የሚሲዮን መሪዎች አይነተኛ ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ፡፡
ሦስተኛ ሣምንቱን ባስቆጠረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች፣ ሚሲዮን መሪዎች እና ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ስልጠና ላይ ብሔራዊ ሀገራዊ ምክክር ላይ ገለፃ ተደርጓል።
ገለፃውን ያደረጉት የኮሚሽኑ አባል ዶ/ር ተገኘወርቅ ጌጡ በቀጣይ በሚደረገው ምክክር ላይ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ከሚገኙ የዳያስፖራ አካላት ጋር ውይይት እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡
ይህንንም ለማከናወን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው የሥልጠና ውሎ በፓርላማ ዲፕሎማሲ፣ በሽግግር ፍትህ እንዲሁም በውጭ አገር የሥራ ስምሪት ዙሪያ ገለፃ ተሰጥቷል።
በፓርላማ ዲፕሎማሲን በተመለከተ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ዲማ ነገዎ ገለፃ አድርገዋል፡፡
የሽግግር ፍትህን አስመልክቶ በፍትህ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ማብራሪያ መሰጠቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን በተመለከተም ከስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በመጡ የስራ ሃላፊዎች ገለፃ ተሰጥቷል፡፡