የተጀመረው የሰላም ተስፋ እንዲጸና አባታዊ ሃላፊነታችንን እንወጣለን- የትግራይ ክልል የሃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተጀመረው የሰላም ተስፋ እንዲጸና አባታዊ ሃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉ የትግራይ ክልል የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡
ፋና ብሮድካስንቲግ ኮርፖሬት በሽራሮ፣ አክሱምና አድዋ ከተሞች ያነጋገራቸው የክርስትና እና እስልምና ሃይማኖት አባቶች ÷ሰላምን መስበክ በየሃይማኖቶቹ ተቀባይነት ያለው ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላምም ሁሉም ሊጠብቀውና ሊንከባከበው ይገባል ነው ያሉት፡፡
አዎንታዊ የሃይማኖት እሴቶችን ለምዕመናን በማስተማርም ጦርነት በዘላቂነት ቆሞ ሰላም እንዲጸና እንሰራለን ብለዋል የሃይማኖት አባቶቹ።
የሰላም መደፍረስ በዓብያተ እምነቶች እና ምዕመናን ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ አስቀድሞ ስለሰላም በመስራት ማስቆም ይገባል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶቹ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ እየተሰሩ ያሉ የመሰረታዊ አገልግሎት፣ የሰላምና ፀጥታ፣ የሰብዓዊ እርዳታ ስራዎች አዎንታዊ ጅምሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ስለሆነም የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና በሁሉም አካባቢዎች በፍጥነት ተደራሽ እንዲሆኑ እንዲሰራ ጠይቀዋል።
የሃይማኖት አባቶች ከየትኛውም ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ገለልተኛ በመሆን ሰላም እንዲጸናና ዜጎች ወደመደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ አባታዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶቹ አሁን ላይ ምዕመናንን የማረጋጋትና የማስተማር ስራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ