ሩሲያ በዩክሬን ፕሬዚዳንት ትውልድ ከተማ ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟ ተሰማ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ትውልድ ከተማ ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟ ተሰምቷል፡፡
የሩሲያ ጦር በማዕከላዊ ዩክሬን በምትገኘው ክሪቪ ሪህ ከተማ ላይ በፈጸመው የሚሳኤል ጥቃት እስካሁን የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ባላስልጣናት ተናግረዋል።
እንደ ከተማዋ ባለስልጣናት ገለጻ ÷ዛሬ ጠዋት አካባቢ በመኖሪያ ህንጻ ላይ በተጸፈመው ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች ቀላል እና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷በጥቃቱ ለህልፈት ለተዳረጉ ዜጎች ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
“ዩክሬን ምን ጊዜም ለሩሲያ እጅ አትሰጥም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ “ለእያንዳንዷ የሚሳኤል ጥቃትም ሞስኮን ተጠያቂ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
በዛሬው ዕለት የተፈጸመውን የሚሳኤል ጥቃት አስመልክቶ በሩሲያ በኩል የተሰጠ አስተያየት አለመኖሩን አልጀዚራ በዘገባው አስፍሯል፡፡