የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን “ጎልደን ሪሴፕሽን” የተሰኘ አገልግሎት አስጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን “ጎልደን ሪሴፕሽን” የተሰኘ አገልግሎት በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል፡፡
የ”ጎልደን ሪሴፕሽን” አገልግሎት በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስተሮች ስራቸውን ለመከታተል ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከአየር መንገድ ጀምሮ የሚደረግላቸው የ”ቪ አይ ፒ” አቀባበል ስነ-ስርዓት መሆኑ ተገልጿል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ባለሃብቶች በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት በማድረግ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በኤክስፖርት ምርት፣ ተኪ ምርት እና በሌሎች የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ፕሮግራሙ ኢንቨስተሮች በሚመጡበት ወቅት ከኮርፖሬሽኑ የበላይ ኃላፊዎች በተጨማሪ በየወቅቱ ኢንቨስተሮቹ ካላቸው ቢዝነስ ጋር ተያያዥ የሆኑ አገልግሎት ሰጪ የመንግስት ተቋማት ኃላፊዎች ጭምር አቀባበል እንዲያደርጉ በማሰብ የተዘጋጀ መሆኑ ተጠቅሷል።
በዚሁ መሰረት ኢንቨስተሮቹ ወደ ሀገር ሲገቡ ልዩ መግቢያ (ቪ አይ ፒ ) እንዲመቻችላቸው እና ከአየር መንገድ እስከ ሆቴልና ማረፊያቸው ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎት በተቋሙ ሃላፊ አሽከርካሪነት እንዲሰጣቸው ይደረጋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የተቋሙ የበላይ ሃላፊዎችም የክብር እጅባ እንዲያደርጉላቸው የሚደረግ ሲሆን÷በቆይታቸው ሁሉ የትራንስፖርት አገልግሎት እና የሆቴል መስተንግዶ እንዲያገኙ እንዲሁም የኢትዮጵያን ባህላዊ የቡና ስነ-ስርዓት እንዲጋበዙ የሚያስችል አገልግሎት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በዛሬው ዕለትም በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በምርት ሂደት ላይ የሚገኘው የሺንትስ ኩባንያ ፕሬዚዳንት እና ባለቤት ቻ ሚን ሆ ከትዳር አጋራቸው ኬዩም ሺክ ጋር ኢትዮጵያ ሲገቡ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ሺንትስ የጨርቃ ጨርቅና ጋርመንት ኩባንያ መሰረቱን ደቡብ ኮርያ ያደረገ ሲሆን÷በፈረንጆቹ በ2014 በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ በመጀመር ከ5 ሺህ በላይ ሰራተኞችን ቀጥሮ እያሰራ እንደሚገኝ የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡