ኢትዮጵያ ፍልሰተኞችን በማስተናገድ ዓለም አቀፋዊ ግዴታዋን እየተወጣች ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ ፍልሰኞችን ተቀብላ በማስተናገድና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ዓለም አቀፋዊ ግዴታዋን እየተወጣች ነው አሉ ።
ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ “ፍልሰተኞችን እናክብር፣ የወደፊት ህይወታቸውን በጋራ እንቅረፅ” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ዕለት ተከብሯል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ የፍልሰተኞች መተላለፊያና መኖሪያ ሀገር በመሆን ዓለም አቀፋዊ ግዴታዋን እየተወጣች ትገኛለች።
በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ከባቢያቸውን የሚለቁ ፍልሰተኞች ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተጋለጡ በመሆናቸው ክብካቤ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት።
የፍልሰተኞች ጉዳይ በትክክል ከተመራና በቅንጅት ከተሰራ ለሀገር ልማት፣ ለፈጠራ፣ ለማኅበረሰብ እድገትና በመሰል ትሩፋቶች ሰፊ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አስረድተዋል።
ፍልሰተኞች በሀገር ልማት ላይ ያላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እየተሰራ ስለመሆኑም አመልክተዋል።
የፍልሰት ተመላሾችን በተጠናና ዘላቂ በሆነ መልኩ በማቋቋምና መልሶ ወደ ማኅበረሰቡ በመቀላቀል የተለወጠ ሕይወት እንዲኖሩ ለማድረግ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሆነ ገልጸው፥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በለይኩን ዓለም