ጎንደር የምትጠብቀው ሰው ሰራሽ ሀይቅ እውን ሊሆን ተቃርቧል
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት አማካኝነት በጎንደር የሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ እውን ሊሆን ተቃርቧል፡፡
870 ሄክታር መሬት በሚሸፍን ቦታ ላይ ያረፈው የመገጭ ግድብ 180 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ የመያዝ አቅም አለው፡፡
በግድቡ አማካኝነት ወደኋላ የሚተኛው ውሀ ከ5 እስከ 7 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፥ ይህም ጎንደር ከተማን የሰው ሰራሽ ሀይቅ ባለቤት እንድትሆን የሚያደርጋት ነው።
በሰኔ ወር መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ፕሮጀክቱ 77 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፥ ግንባታው ሲጠናቀቅ በመስኖ ብቻ 17 ሺህ ሔክታር መሬት ያለማል።
ከተጀመረ ከ15 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች እየተጓተተ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።
በ2016 ዓ.ም የመጨረሻዎቹ ወራት ከተላለፈው ቆራጥ የአመራር ውሳኔ ወዲህ ፕሮጀክቱ እጅግ ፈጣን በሆነ የአፈጻጸም ሂደት ላይ ይገኛል።
ግንባታውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚያስችለው የውሀ ቅልበሳ ስራ ከወር በፊት በስኬት ተጠናቋል።
ግንባታውን ካለፈው ዓመት ጀምሮ እያከናወነ የሚገኘው ሀገር በቀሉ ድርጅት ቤአኤካ ስራውን በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ በየዕለቱ ለ24 ሰዓታት በፍጥነትና በጥራት እየሰራ ይገኛል።
በቤአኤካ ኮንስትራክሽን የመገጭ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ጌታቸው አረጋ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደተናገሩት፥ በተለይም መሰረታዊ የግንባታ ምዕራፎችን በስኬት ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡
ውሀውን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የማፋሰስ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የፕሮጀክቶች ፕሮግራም ጽ/ቤት ኃላፊ አሸናፊ ካሳ በበኩላቸው አሁን ላይ የፕሮጀክቱ ግንባታ 77 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለጎንደር እና በጎንደር ዙሪያ ለሚገኙ ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውኃ አገልግሎት ለማቅረብ ያስችላልም ነው ያሉት፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እንዳሉት፥ በግድቡ አማካኝነት የሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ ጎንደር ለአዲስ የቱሪዝም አማራጭ ራሷን እንድታዘጋጅ አድርጓል፡፡
በቀጥታ ከሚፈጠረው ሀይቅ ዳርቻ የሚያገናኝ የአስፓልት መንገድ እየተሰራ ሲሆን፥ በሀይቁ ዙሪያ አዳዲስ ሎጆችን መገንባት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በሀይቁ የአሳ ልማትን ማከናወን እንደሚቻል ገልጸው፥ ይህም ተጨማሪ የቱሪዝም አማራጭና ሰፊ የስራ እድል ይዞ ይመጣል ነው ያሉት፡፡
የመገጭ መስኖ ልማት ፕሮጀክትን በዚህ ዓመት ከሰኔ 30 በፊት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው።
በአሸናፊ ሽብሩ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!