Fana: At a Speed of Life!

አምራች ኢንዱስትሪን ለማዘመን የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሚና ወሳኝ ነው – አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንዱትሪ ሚኒስቴር የበላይነት የሚመራው የፌዴራል የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ስትሪንግ ኮሚቴ የስራ አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የኢንቨስትመት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ፣ የክልል የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኃላፊዎች እና አጋር የልማት ድርጅት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

የውይይት መድረኩ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉበትን ደረጃ ገምግሞ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

አቶ መላኩ አለበል÷ እንደ ሀገር ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ የአምራች ኢንዱስትሪን ለማዘመን የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሚና ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዘርፉ የሚሰማሩ አዳዲስ ባለሃብቶችን ከመሳብ፣ የእሴት ሰንሰለትን በመጨመር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከመቅረፍና ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት ከመስራት አንጻር ጥሩ አፈጻጸም መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

የፓርኮቹ ቀሪ መሰረተ ልማት የሚጠናቀቅበት፣ የማስተዋወቅ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት፣ የእሴት ሰንሰለትን ማሳደግ እና የፋይናንስ ተደራሽነትን ከማሳደግ አንጻር እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የአቅም ግንባታ ስራዎች ከማጠናከር እና ቅንጅታዊ አሰራሮችን ከማሳደግ አንጻር ግልጽ የሆነ የቀጣይ ጊዜ እቅድ በፓርኮቹ አመራሮች ተዘጋጅቶ ወደ ስራ እንዲገባ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

አጋር አካላትም እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ መቅረቡን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.