የልማት ስራዎች መዲናዋን የስበት ማዕከል አድርገዋታል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች በከተማዋ የተሰሩ የልማት ስራዎች ከተማዋን የስበት ማዕከል አድርጓታል አሉ።
አዲስ አበባ የአደባባይ በዓሎችንና ትላልቅ ኹነቶችን የማስተናገድ አቅሟን እንዲሁም መስተንግዶዋ ዓለም አቀፋዊ ደረጃን መያዝ የሚችል ስለመሆኑ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች በዛሬው ዕለት ገምግመዋል።
በዚህም አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኹነቶች፣ የአደባባይ ክብረ በዓላት በተከታታይ ከፍ ባለ ሥነ ሥርአት፣ ደማቅ እና ስኬታማ ሆነዉ መከናወናቸውን አይተዋል።
ይህም ከተማዋ የትኛዉንም ኹነት በብቃት የማስተናገድ ችሎታዋ እያደገ መምጣቱን እንደሚያሳይ ተመላክቷል።
ለዚህም በከተማዉ የተሰሩ የልማት ስራዎችና መሰረተ ልማቶች ወደ አደባባይ ለሚተመዉ ነዋሪ እና ጎብኚ የሚፈጥሩት ተጨማሪ ውበት እና ምቾት አዲስ አበባን የስበት ማዕከል ማድረጉ ተገልጿል።
ልማቶቹ በከፍተኛ ሁኔታ የከተማዋን ኢኮኖሚ ያነቃቃና የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ማድረጉን የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃፍታይ ገብረእግዚአብሔር ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች ከተማዋ ያስመዘገበችው ስኬት ለኢትዮጵያ ትልቅ የአብሮነት እና የማንሰራራት መሰረት በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በከተማዋ የሚካሄዱ መርሐ ግብሮች በስኬት እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
በቅርቡ 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ፣ የአፍሪካ ካረቢያን መሪዎች ጉባኤ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ፣ የመስቀል ደመራ እና ሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል መስተናገዳቸው ይታወቃል።