በጋምቤላ ክልል በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 3 ሚሊየን ችግኞች ይተከላሉ- አቶ ኡሞድ ኡጅሉ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በአንድ ጀምበር ሶስት ሚሊየን ችግኞችን መትከል የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ኡሞድ ኡጅሉ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ የሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ላይ የክልሉ ሕብረተሰብ ተሳትፎውን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።
በዚህም እስካሁን 2 ነጥብ 5 ሚሊየን የችግኝ መትከያ ጉድጓድ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች መቆፈሩን ጠቅሰው÷ በቀጣይ ቀናት ቀሪዎቹ ጉድጓዶች እንደሚዘጋጁ አመላክተዋል።
በዘንድሮው ዓመት የሚተከሉት ችግኞች በአብዛኛው ለምግብነት የሚውሉ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውም ነው የተናገሩት።
ይህም እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብርን ለማጠናከር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብሩ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በክልሉ በአንድ ጀምበር ሶስት ሚሊየን ችግኝ ለመትከል የተያዘውን ግብ ለማሳካት ሁሉም የክልሉ ሕዝብ በዕለቱ በነቂስ ወጥቶ በመርሐ-ግብሩ ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።