Fana: At a Speed of Life!

ከ9 ሚሊየን በላይ ብር ታክስ መንግስትን አሳጥተዋል የተባሉ ግለሰቦች በሙስና ወንጀል ተከሰሱ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ9 ሚሊየን በላይ ብር ዓመታዊ የገቢ ግብር ታክስ መንግስትን አሳጥተዋል የተባሉ ሦስት ግለሰቦች በሙስና ወንጀል ተከሰሱ።

ተከሳሾቹ 1ኛ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርታለች የተባለችው ተቋራጭ አብዬ አማረ፣ 2ኛ የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ የሒሳብ ባለሙያ ተረፈ ቦጃ እና 3ኛ የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ የግብር ክትትል ቡድን መሪ መንግስቱ ሙሉነህ ናቸው።

የኦሮሚያ ፍትሕ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ሁለት የወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 33 እንዲሁም ሙስናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል ተብለው ነው የሙስና ወንጀል ክስ የቀረበባቸው።

1ኛ ተከሳሽ የታክስ አስተዳደር አዋጁን በመተላለፍ ዓመታዊ የግብር ገቢ መክፈል ሲገባት የከፈለች ለማስመሰል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠመንጃ ያዥ ቅርንጫፍ የተሰጠ የሚመስል ሀሰተኛ የኦሮሚያ ገቢዎች ሒሳብ ያልሆነ የባንክ ስሊፕ ማቅረቧ በክስ መዝገቡ ላይ ተመላክቷል፡፡

2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችም ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር ያቀረበችውን ሐሰተኛ የባንክ ስሊፕ ሕጋዊነት ማረጋገጥ ሲገባቸው÷ ሳያረጋግጡ ስሊፑን እና ሌሎች ሐሰተኛ ሠነዶችን በመቀበል ግለሰቧ የገቢ ግብር ከፍላለች ሲሉ ደረሰኝ መስጠታቸው ተጠቅሷል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ መንግስትን 9 ሚሊየን 292 ሺህ 127 ብር ከ83 ሳንቲም ገቢ አሳጥተዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎትም የቀረበውን ክስ ለመመልከት ለነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.