ጾታዊ ጥቃትን በመከላከል የሴቶችን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ መስራት ይገባል- ፕሬዚዳንት ታዬ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለሴቶችና ሕጻናት ደህንነት ዋስትና የምትሰጥ የፍትሕና እኩልነት ተምሳሌት ሀገር እንድትሆን ሁሉም በትኩረት ሊሰራ ይገባል አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።
“ጥቃትን የማይታገስ ማሕበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ ላለፉት 16 ቀናት ሲከበር የቆየው የጸረ ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃት በአካላዊና አእምሯዊ ጤንነትና ደህንነት እንዲሁም በሁሉም የሕይወታቸው ደረጃ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡
በቤተሰብ፣ በሕብረተሰብ ብሎም በሀገር ላይ መጠነ ሰፊ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በማስከተል ዘላቂ ልማት እንዳይረጋገጥ እንቅፋት እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡
ስለሆነም ኢትዮጵያ ለሴቶችና ሕጻናት ደህንነት ዋስትና የምትሰጥ የፍትሕና እኩልነት ተምሳሌት ሀገር እንድትሆን ሁሉም በትኩረት ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በተለይም ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከልና ለማስቆም የፍትሕ ሥርዓቱን ማዘመን፣ የተደራሽነትና የግልጸኝነት ልኬትን ማበጀት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ሕጻናት ድጋፍ ለመስጠት የአንድ ማዕከል አገልግሎትና ማረፊያዎችን ለማቋቋምና ለማስፋፋት የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ አሰራሮችንና የአገልግሎት ሥርዓቶችን በመዘርጋት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተጎጂዎች ላይ የሚደርሰውን የጤና፣ የማሕበራዊና ሥነ ልቦናዊ እንዲሁም የሕግ ምላሽ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡
በጸሃይ ጉሉማ