ዜጎችን መደበኛ ካልሆነ ፍልሰት ለመጠበቅ ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል – ወ/ሮ ሁሪያ አሊ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዜጎችን መደበኛ ካልሆነ ፍልሰት ለመጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል አሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ሁሪያ አሊ፡፡
ዓለም አቀፉ የፍልሰት ቀን “ፍልሰተኞችን እናክብር፣ የወደፊት ሕይወታቸውን በጋራ እንቅረፅ” በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በነገው ዕለት ይከበራል።
ሚኒስትር ዴዔታዋ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ÷ ቀኑ ዜጎች ሕጋዊ የፍልሰት ሥርዓትን በመከተል ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ለማስገንዘብ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ጎልቶ በሚታይባቸው ክልሎች ሀገራዊ ንቅናቄና የውይይት መድረክ በማዘጋጀት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በስፋት መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ500 ሺህ በላይ የፍልሰት ተጎጂዎችን ከተለያዩ ሀገራት በመመለስ የሥነ ልቦናና የማህበራዊ አገልግሎት ድጋፍ አግኝተው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡
ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ወንጀልን መከላከል የሚያስችል የሆሳዕና ቃል ኪዳን ሰነድ ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡
ከተለያዩ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈረም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን የመከላከልና ተመላሽ ዜጎችን የመደገፍ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያን የፍልሰት አስተዳደር ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ የ5 ዓመት የፍልሰት ስትራቴጂክ ዕቅድ ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ደርጅት ጋር ተፈርሞ ወደ ሥራ መግበቱን ነው ያስረዱት፡፡
ዜጎችን መደበኛ ካልሆነ ፍልሰት ለመጠበቅም መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በጸሃይ ጉልማ