Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የዓለም አየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተቀናጀ ስራ እያከናወነች ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም አየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተቀናጀ ስራ እያከናወነች እንደምትገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

አቶ ደመቀ በ78ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡

በተለይም የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች እና የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትን ገቢራዊ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ሰላም እና ፀጥታ፣ ዘላቂ የልማት ግቦች፣ የዓለም የአየር ንብረትን በንግግራቸው አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት እቅዷን ከተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች ጋር አጣጥማ በመቅረፅ እየተገበረች መሆኗምን ጠቁመው÷ የዓለም አየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምም የተቀናጀ ስራ እያከናወነች እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን አንስተው÷ በገጠር እና ከተሞች አካባቢ የልማት ስራዎችን በማስፋፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

በፈረንጆቹ 2030 ለማሳካት የታቀዱት ዘላቂ የልማት ግቦች የእስካሁን አፈፃፀማቸው አመርቂ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በቀሩት ጊዜያት የተሻለ ስኬት እንዲኖር የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና አዲስ ዓለም አቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የዓለም አየር ንብረት ለውጥ በአዳጊ ሀገራት ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት እስከ 2030 ድረስ 100 ቢሊየን ዶላር ለማሰባሰብ የተቀመጠው እቅድ እየተሳካ እንዳልሆነም ነው ያነሱት በንግግራቸው፡፡

በቀጣይ በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በሚካሄደው የዓለም አየር ንብረት ጉባኤ ሀገራት ተግባራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ቁርጠኝነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለተልዕኮው ስኬታማነት ተቋማዊ ማሻሻያን ማድረግ አማራጭ ሳይሆን አስፈላጊ ነው ብላ ኢትዮጵያ እንደምታምንም አስረድተዋል፡፡

አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀጫ እንዲኖራት በአህጉር ደረጃ የተያዘው አቋሞ ተገቢ ስለመሆኑም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ድኅረ ፕሪቶሪያ ያለውን የሰላም ስምምነት አተገባበር ያነሱት አቶ ደመቀ÷ ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ ለማድረግም መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የሽግግር ፍትሕን ለማረጋገጥም ፖሊሲ በማርቀቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምክክር እንደተደረገ አስታውቀው÷ እርቅን፣ እውነትን ለማፈላለግ እና ተጠያቂነትን እውን ለማድረግ መንግስት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በሰላም እና ልማት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ አጠናክራ የማስቀጠል ፍላጎት እንዳላት ያነሱት አቶ ደመቀ÷ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የጋራ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ ነች ብለዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአካባቢው ሀገራት ዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል የሚያግዝ ተምሳሌታዊ የልማት ኘሮጀክት እንደሆነም አቶ ደመቀ መኮንን አንስተዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.