Fana: At a Speed of Life!

መዲናዋን የሚመጥን የደንብ ማስከበር ሥራ ለማከናወን…

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከተማዋን የሚመጥን የደንብ ማስከበር ሥራ ለማከናወን በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው አለ፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በአዲስ አበባ የሚስተዋሉ የተለያዩ ደንብ ጥሰቶችን ለመከላከል ከባለድርሻዎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ላይ ይገኛል።

የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ አሁን ላይ የደረሰችበትን ደረጃ የሚመጥን የደንብ ማስከበር ሥራ ለማከናወን ትኩረት መደረጉን አመልክተዋል፡፡

ባለፉት 6 ወራት በሕገ ወጥ ግንባታ፣ በመሬት ወረራ፣ በሕገ ወጥ ንግድ፣ በአዋኪ ተግባራት፣ በሕገ ወጥ ማስታወቂያና እርድ እንዲሁም ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት ላይ አስፈላጊው ቁጥጥር መደረጉን ተናግረዋል።

እንዲሁም በመዲናዋ የተከናወኑት የኮሪደር እና ወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች ላይ የሚስተዋሉ የደንብ መተላለፍ ተግባራትን ለመከላከል በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በዚህም በ2017 በጀት ዓመት ከነበረው የደንብ ጥሰት 87 በመቶ መቀነስ መቻሉን ጠቁመው÷ በተለይም ሕገ ወጥ ግንባታ፣ የመሬት ወረራና ሕገ ወጥን ንግድ ላይ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል፡፡

ለደንብ መከላከል ሥራው ውጤታማነት የቅድመ መከላከል እና በህብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠረው ግንዛቤ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት፡፡

ዘመኑን የዋጀ የደንብ ማስከበር ሥራ ለማከናወን በትኩረት መሰራቱን ጠቅሰው ÷ በዚህም በሥነ ምግባር የታነጸና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።

ለአብነትም ከ8 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኦፊሰሮች በኢትዮጵያ ፓሊስ ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂ፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ በተግባቦት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በብልሹ አሰራርና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና መጠናቀቁን ጠቅሰዋል፡፡

ሥልጠናው የአዲስ አበባን እድገት የሚመጥን እና የባለስልጣኑን ተልዕኮ በሚገባ መወጣት የሚችል አመራርና ኦፊስር በማፍራት ረገድ ከፍተኛ እግዛ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

አዲስ አበባ ለኑሮ ምቹና ውብ ከተማ ሆና እንድትቀጥል የሚስተዋሉ የደንብ ጥሰቶችን በመከላከል ረገድ ሕብረተሰቡ፣ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.