Fana: At a Speed of Life!

ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ፌሮ ብረት ከቀረጥ ነጻ አስገብቷል የተባለ ግለሰብ በሙስና ወንጀል ተከሰሰ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ፌሮ ብረት ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቷል የተባለው ግለሰብ ላይ ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ተረኛ ችሎት ነው።

ዮሴፍ ዳዊት ሖማ የተባለው ተከሳሽ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ሲቲ ከተማ ቡራዩ ክ/ከተማ ነዋሪ ሲሆን÷ የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀሎች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ሁለት ተደራራቢ ክሶችን አቅርቦበታል።

በአንደኛው ክስ ላይ ተከሳሹ በ2008 ዓ.ም የወጣውን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር- 980/2008 በአንቀፅ- 49 ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተደነገገውን ድንጋጌ ተላልፏል የሚል ክስ ነው የቀረበበት።

ተከሳሹ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማቅረብ፣ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ለማውጣት መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ/ም ለኢትጵያ አንቨስትመንት ኮሚሽን ዋይኤ ሆቴል ኤንድ ሪዞርት ኃላ/የተ/የግ/ማህበር በሚል ስያሜ በውጪና በሀገር ውስጥ ባለሃብት ቅንጅት ለማቋቋም እና ድርጅቱን በስራ አስኪያጅነት ለመምራት የንግድ ምዝገባ ማመልከቻ ማቅረቡን ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።

ኮሚሽኑ ማመልከቻውን በመቀበል የሚቋቋመውን ድርጅት የአቅም ማሳያ የሚሆን የተከፈለ ካፒታል እና በማህበሩ ስም በውጭ ምንዛሬ አካውንት የተቀመጠ ገንዘብ ከባንክ እንዲያቀርብ መጠየቁም በክሱ ተመላክቷል።

ተከሳሹ በመስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ከአዋሽ ባንክ በተጠቀሰ ሂሳብ ቁጥር ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተጻፈና በሆቴሉ ስም ተከፍቶ በሂሳብ ቁጥር 7 ሚሊየን 890 ሺህ ብር ገቢ የተደረገ መሆኑን የሚገልፅ የባንክ ሰነድ ማቅረቡ በክሱ ላይ ተጠቅሷል።

በተመሳሳይ ቀን ከአዋሽ ባንክ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንደተፃፈ የሚገልፅ ዋይኤ ሆቴል ኤንድ ሪዞርት ኃላ/የተ/የግ/ማህበር ሥም በተከፈተ የውጭ ምንዛሬ አካውንት ደግሞ 150 ሺህ ዶላር ገቢ መሆኑን የሚገልፅ የባንክ ሰነድ ማቅረቡ በክሱ ተዘርዝሯል።

ተከሳሹ ይህንን ሰነድ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በአካል ያቀረበ መሆኑን የጠቀሰው ዐቃቤ ህግ ተከሳሹ ከአዋሽ ባንክ ያቀረባቸውን የአቅም ማሳያ የሆኑትን የባንክ መግለጫዎችን እና ሌሎች ሰነዶችን ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከተከሳሽ ተቀብሎ ተከሳሹ በሥራ አስኪያጅነት የሚያስተዳደረውና ዋይኤ ሆቴል ኤንድ ሪዞርት ኃላ/የተ/የግ/ማህበር በሚል የንግድ ድርጅት ስያሜ በንግድ ፈቃድ ቁጥር የንግድ ምዝገባ ምስክር ወረቀትና የውጭ ባለሃብት የኢንቨስትመንት ፈቃድ በጥቅምት 4 ቀን በቀን 2015 ዓ.ም የሰጠው መሆኑ ተመላክቷል።

ነገር ግን ተከሳሹ የንግድ ምዝገባውን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለማከናወን ከአዋሽ ባንክ ያቀረባቸው የአቅም ማሳያ የባንክ ሰነዶች ከባንኩ ያልተሰጡና ሀሰተኛ ማስረጃዎች መሆናቸው የተረጋገጠ በመሆኑ፤ በፈፀመው ሀሰተኛ የንግድ ምዝገባ ማስረጃዎችን በማቅረብ በንግድ ምዝገባ መመዝገብ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።

በሁለተኛው ክስ ደግሞ ዐቃቤ ህግ በተከሳሹ ላይ በ2007 ዓ .ም የወጣውን የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 በአንቀፅ 23 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እንዲሁም ንዑስ ቁጥር 2 እና 3 ስር የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦበታል።

በ2ኛው ክስ እንደተመላከተው ተከሳሹ ሀሰተኛ የአዋሽ ባንክ ማስረጃዎች በማቅረብ ዋይኤ ሆቴል ኤንድ ሪዞርት የሚባል የንግድ ድርጅት ካስመዘገበ እና የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወጣ በኋላ በድርጅቱ ስም ባለ ኮኮብ ደረጃ ሆቴል ለማስገንባት ቅድመ ሁኔታዎችን እንደጨረሰና ለግንባታውም 8 ሺህ 500 ቶን ፌሮ ብረት እንደሚያስፈልገው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የአገልግሎት ፕሮጀክቶች ማበረታቻ ክፍልን መጠየቁ በክሱ ዝርዝር ተገልጿል።

የፌሮ ብረቱንም ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲገባ እንዲፈቀድለት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የቂርቆስ ክ/ከተማ ጽ/ቤት በይዞታ መለያ ቁጥር እና የሴሪ ቁጥር የተጠቀሰበት በመጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ዋይኤ ሆቴል ኤንድ ሪዞርት ለተባለ ድርጅት እንደተሰጠ የሚገልፅ የመሬት ይዞታ መብት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ማቅረቡም ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።

በተጨማሪም ÷ተከሳሹ ከአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በቁጥር በጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ/ም በዋይኤ ሆቴል ኤንድ ሪዞርት ኃላ/የተ/የግ/ማህበር ለተባለ ድርጅት ለሆቴል አገልግሎት ባለ 12 ወለል ሕንጻ ለመገንባት የግንባታ ፈቃድ ምስክር ወረቀት እንደተሰጠው የሚገልፅ ሰነድ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ሰነዶችን በማያያዝ በታህሳስ ወር 2015 ዓ.ም ማመልከቱ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለሆቴሉ ግንባታ ያስፈልጋል በማለት ተከሳሹ ካቀረበው የብረት መጠን ውስጥ በመጀመሪያ ዙር 1 ሺህ 500 ቶን ባጠቃላይ 40 ሚሊየን 665 ሺህ 842 ብር ከ41 ሳንቲም ቀረጥና ታክስ ሊያስከፍል የሚችል ፌሮ ብረት ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲያስገባ እንዲፈቀድለት ለገንዘብ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ መሰረት ተከሳሹ 256 በንድል ብረት በድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ መሆኑ ተመላክቷል።

ነገር ግን ተከሳሹ የተጠቀሰውን ፌሮ ብረት ከቀረጥና ታክስ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እንዲፈቀድለት ያቀረባቸው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እና የግንባታ ፈቃድ የምስክር ወረቀት ሐሰተኛ መሆናቸው መረጋገጡን ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ ዘርዝሯል።

በመሆኑም ተከሳሹ በፈፀመው መንግስታዊ ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት ወይም በሀሠተኛ ሰነድ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል፡፡

ተከሳሹ ተረኛ ችሎት ቀርቦ ክሱ እንዲደርሰው የተደረገ ሲሆን÷ በቀረበበት በክስ ላይ የዋስትና ክርክር ለማድረግ እንዲያስችል ለጥቅምት 2 ቀን ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.