Fana: At a Speed of Life!

ለወጣቶች የምትመች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየመከርን ነው – የጉባዔው ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለወጣቶች የምትመች፣ የተረጋጋችና በጋራ መግባባት የተመሰረተች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተካሄደ ያለው ምክክር ታሪካዊ ሚና እየተጫወተ ነው አሉ በኢትዮጵያ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የተሳተፉ ወጣቶች።

ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጣው ተመካካሪ ወጣት አደም ሳሌ እንደሚለው ÷ የምክክሩ ሂደት ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ሌሎች የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በስፋት ያሳተፈ አካታች መድረክ ነው።

በምክክሩ የሀገር ግንባታ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እየተፈጠረ እንደሚገኝ ገልጾ÷ ይህም ሀገራዊ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ጉልህ አስተዋፅኦ አለው ብሏል።

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመጣችው ተመካካሪ ወጣት ሊዲያ ኬሮ በበኩሏ÷ ምክክሩ በብሔር፣ በሐይማኖት፣ በፆታና በማንነት የተለያዩ ዜጎችን በአካታች ሁኔታ በማሳተፍ ልዩነቶችን ወደ መግባባት እየቀየረ መሆኑን ተናግራለች።

ኢትዮጵያ እንደ ሀበሻ ቀሚስ ናት፤ ውበቷ በተለያዩ ቀለሞች እንደሚገለጽ ሁሉ የሀገራችንም ጥንካሬ ያለው በልዩነቶቿ ውስጥ በሚገኝ አንድነት ነው ብላለች።

የአሁኑ ትውልድ በምክክሩ ያሳየው ተሳትፎና መስዋዕትነት ለሚቀጥለው ትውልድ የተሻለችና የተረጋጋች ኢትዮጵያ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ የሚጥል ታሪካዊ ርምጃ መሆኑን ነው ያብራራችው።

ምክክሩ በተደራጀና በአካታች መልኩ መካሄዱ የተሳታፊዎች የጋራ ውይይት ለሀገር ግንባታ የጋራ ኃላፊነትን ለማጎልበት ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ያለው ደግሞ ከጋምቤላ ክልል የመጣው ተመካካሪ ወጣት ቾል ፑግ ነው።

ሰዎች ችግሮቻቸውን በመወያየትና የጋራ መፍትሔ በማፈላለግ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን እንደሚችሉም ነው ወጣቱ ያስረዳው።

የድሬዳዋው ወጣት ተመካካሪ አሕመድ ሁሴን ÷ በሀገራዊ ምክክሩ መሳተፉ የሀገሪቱን ችግሮች በጋራ ለይቶ በመወያየት ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ በሚደረገው ታሪካዊ ጥረት አካል እንደሆነ እና ተግባራዊ መፍትሔ የሚያስቀምጥ ውጤታማ ምክክር እንደሚኖር ያለውን እምነት ገልጿል።

ተሳታፊዎቹ ምክክሩ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት፣ የጋራ ራዕይ ለመገንባት፣ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለማጠናከርና ለቀጣይ ትውልድ የተረጋጋች፣ የተባበረች እና በሰላም የምትሻገር ኢትዮጵያ ለመገንባት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።

ተሳታፊዎቹ ምክክሩ በሚገባቸው ቋንቋ ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲያቀርቡ ዕድል መፍጠሩን ገልጸው÷ ይህም በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባትን ለማጠናከር ወሳኝ ዕድል የፈጠረ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.