Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ሀገራት በወታደራዊ መስኩ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትስስር ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናት የካበተ የሠራዊት ግንባታ ያላት በመሆኑ ከሀገሪቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሰሩ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ገለጹ።

116ኛውን የመከላከያ ሠራዊት ቀንን አስመልክቶ የሠራዊቱን ታሪክ፣ ተጋድሎና አሁን የደረሰበትን አስተማማኝ ቁመና የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለህዝባዊ እይታ ቀርቧል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የወታደራዊ ታሪክ ቅርስ ጥናትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ተወካይ ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል አግዘው አልታየ፥ አውደ ርዕዩ የሠራዊቱን የጀግንነት ታሪክና አሁን የደረሰበትን አስተማማኝ ቁመና የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ሠራዊቱ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የከፈለውን ዋጋ እና ታሪካዊ ጀግንነቱን መዘከርም የአውደ ርዕዩ ዋና ዓላማ እንደሆነም ነው ያብራሩት።

የተዘጋጀውን አውደ ርዕይ ለመታደም የመጡት የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ታሪክ በጥልቀት እንድንረዳ ያስቻለን ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያና በአፍሪካ ሕብረት የዚምባቡዌ ወታደራዊ አታሼ ብርጋዴር ጄኔራል ኢኔስ አሻሙ፥ አውደ ርዕዩ ስለ ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታሪክ የነበራቸውን ግንዛቤ የሚያሳደግ ሆኖ እንዳገኙትም ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያና ዚምባቡዌ በወታደራዊ መስኩ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው፥ ሀገራቱ በዘርፉ ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የጋቦን ወታደራዊ አታሼ ኃላፊ ኮሎኔል አርስቲዴ አንጉሌት በበኩላቸው፥ አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የገዘፈ ታሪክ ባለቤት መሆኑና የሠራዊቱን ሁለገብ እድገት የታየበት ስለ መሆኑም ነው ያብራሩት።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያለው እምቅ አቅም ለአፍሪካ ሀገራትም ምሳሌ መሆኑን አውስተው፥ ጋቦን እና ኢትዮጵያ በወታደራዊ ዘርፉ ያላቸውን ትስስር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.