Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋ ነዋሪዎች የቱሪዝም ሀብቶችን በማስተዋወቅ የቱሪዝም አምባሳደር ሊሆኑ ይገባል ተባለ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመዲናዋ ነዋሪዎች የቱሪዝም ሀብቶችን አውቀው በማስተዋወቅ የቱሪዝም አምባሳደር ሊሆኑ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ቢሮው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በመተባበር በዓለም ለ44ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ36ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን የዘንድሮው የአለም የቱሪዝም ቀንን አስመልክቶ ልዩ የጥያቄና መልስ ውድድር ተካሂዷል፡፡

የአዲስ አበባን የቱሪዝም ሀብቶች ማስተዋወቅ ዓላማው ባደረገ ልዩ የጥያቄና መልስ ውድድር ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል።

በውድድሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር)÷ ሁሉም ነዋሪ የቱሪዝም ዕውቀት ኖሮት ጎብኚዎችን በሚገባ በማስተናገድና የቱሪዝም ሀብቶችን አውቆ በማሳወቅ የቱሪዝም አምባሳደር ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ቢሮው የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻዎች በሚገባ የማስተዋወቅና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቱሪዝም ዕውቀትን ለማስጨበጥ የጥያቄና መልስ ውድድሩ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በውድድሩ 1ኛ ለወጣ ተወዳዳሪ የ30 ሺህ ብር፣ 2ኛ ለወጣ 20 ሺህ ብርና 3ኛ ለወጣ ተወዳዳሪ የ10 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ሌሎች ተወዳዳሪዎችም ከቢሮው የዕውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።

በዛሬው ዕለት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ስቱዲዮ የተካሄደው ልዩ የጥያቄና መልስ ውድድር በፋና ቴሌቪዥን ለተመልካቾች ይቀርባል፡፡

በመለሰ ምትኩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.