Fana: At a Speed of Life!

የኮቪድ 19 ወረርሽ አስከፊነት ከግምት ያስገባ የጥንቃቄ እርምጃዎች ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- ም/ጠ ደመቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮቪድ 19 ወረርሽ ስርጭት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ የችግሩን አስከፊነት ከግምት ያስገባ የጥንቃቄ እርምጃዎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡

የሚኒስትሮች ኮሚቴ ከኮቪድ-19 አማካሪ ግብረ-ሃይል ጋር በወቅታዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት እና መከላከል ዙሪያ በምስል የተደገፈ ውይይት ተካሄዷል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ የኮቪድ 19 ወረርሽ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ እና አሳሳቢነቱ እየጨመረ በመምጣቱ የፀረ-ኮቪድ 19 እንቅስቃሴ በትኩረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

ከኮቪድ-19 አማካሪ ግብረ-ሃይል አባላት በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚስተዋለው የኮቪድ 19 ወረርሽ ስርጭት በቁጥር እና በፍጥነት አዝማሚያው እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመላው ሃገሪቱ ከተመረመሩት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ከአዲስ አበባ መሆናቸውን የተጠቀሰ ሲሆን በመዲናው ማህበረሰብ ዘንድ ወረርሽኙ በአሳሳቢ ደረጃ ስርጭቱ እየጨመረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽ ስርጭት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ከመዲናዋ በርቀት እና በቅርበት በሚገኙ አከባቢዎች ጭምር አሳሳቢ በመሆኑ ህብረተሰቡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሳይዘናጋ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

መላው ህብረተሰብ የወረርሽኙን ስርጭት አሳሳቢነት በመገንዘብ እጅን በየጊዜው በመታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን ጠብቆ በመንቀሳቀስ እና የፊት ማስክ በመጠቀም ወረርሽኙን እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከኮቪድ-19 አማካሪ ግብረ-ሃይል ሙያዊ ማብራሪያ ተከትሎ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ከኮቪድ-19 የምርመራ ስራው እንዲጠናከር፣ ችግሩን የሚመጥን የህግ ማስከበር ስራ ተግባራዊ እንዲደረግ እንዲሁም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስልጠና ተሰጥቷቸው ህብረተሰቡን የማስተማር ስራ እንዲሰማሩ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.