ከ14 ሺህ ግራም በላይ የኮኬይን እፅ ይዞ የተገኘው ናይጄሪያዊ በጽኑ እስራት ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ14 ሺህ ግራም በላይ ኮኬይን የተሰኘ እፅ ይዞ የተገኘው ናይጄሪያዊ በጽኑ እስራት ተቀጣ፡፡
አሉይሲኡስ ኦኔን የተባለው የናይጄሪያዊ ተከሳሽ ልዩ ፈቃድ ሳይኖረው በሕግ የተከለከሉ እፆችን ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር አስቦ ከብራዚል ሳኦፖሎ ከተማ መነሳቱ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመጠቀም ወደ ናይጄሪያ ሌጎስ ከተማ ለመሄድ ሕዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት ሲሆን ቦሌ አለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ለትራንዚት ባረፈበት ወቅት በተደረ ፍተሻ ሻንጣው ውስጥ ደብቆ 5 እሽግ ወይም 14 ሺህ 319 ነጥብ 69 ግራም የሚመዝን ኮኬይን አደገኛ እፅ እንደተገኘበት ተመላክቷል፡፡
በመሆኑም ሰዎችን ሱስ በማስያዝ ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች መንስኤ እንዲሆኑ ስለሚገፋፋ እንዳይመረት፣ እንዳይዘዋወርና በጥቅም ላይ እንዳይውል የታገደውን ኮኬይን እፅ ፈቃድ ሳይኖረው ይዞ እየተጓዘ የተገኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ዐቃቤ ሕግም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 525/1/ለ/ ስር የተደነገገውን በመተላለፍ አደገኛ እፆችን ማዘዋወር ወንጀል ክስ መስርቶበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ተከሳሹ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ችሎት ቀርቦ የተከሰሰበት ክስ በችሎት ተነቦለት በወቅቱ ይዞት በነበረው ሻንጣ ውስጥ ምንም አይነት ኮኬይን ይዞ እንዳልነበር ገልጿል፡፡
ዐቃቤ ሕግም በጉዳዩ ላይ የሚያስረዱ የሕግ ምስክሮችን አቅርቦ በማሰማት፣ ተከሳሹም በቀረበበት ክስ መሰረት እንዲከላከል ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ መስጠቱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ይሁን እንጂ የመከላከያ ምስክር የለኝም በማለት ባለማቅረቡ የመከላከል መብቱ ታልፎ በቀረበበት ክስ ስር በማስረጃ እንደ ክሱ አቀራረብ የተረጋገጠበት በመሆኑ በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡