Fana: At a Speed of Life!

በጠብመንጃ ሳይሆን፣ በሰለጠነ የፖለቲካ ባህልና በሕዝብ ፍላጎት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በታሪክ ማህደር ውስጥ በጉልበትና በጠብመንጃ አፈሙዝ ስልጣን መያዝ የብዙ ሀገራት መገለጫ ሆኖ ቆይቷል።

ነገር ግን የሰው ልጅ ስልጣኔና የፖለቲካ ንቃተ ህሊና እያደገ ሲሄድ፣ የሀገር መረጋጋትና እድገት የሚረጋገጠው በሃይል ሳይሆን በሕዝብ ፍላጎት መሆኑ እየታመነበት መጥቷል።

የፖለቲካ ስልጣን በጠብመንጃ ሳይሆን በሰለጠነ የፖለቲካ ባሕልና በሕዝብ ምርጫ ላይ መመስረት ያለበት ለምን እንደሆነና ይህንን ባህል እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል መፈተሽ የዛሬው ዘመን ዋነኛ የቤት ስራ ነው።

በጠብመንጃ አፈሙዝ የሚመጣ ስልጣን መቼም ቢሆን ዘላቂ ሰላምን ሊያመጣ አይችልም።

በጉልበት ወንበር ላይ የሚቀመጥ አካል የሕዝብ የልብ ድጋፍ ስለማይኖረው ስልጣኑን ለማስጠበቅ ሁልጊዜም ተጨማሪ ሃይልና ጭቆናን ለመጠቀም ይገደዳል።

በሃይል የመጣን መንግሥት በሃይል ለመጣል የሚነሱ አካላት ስለማይጠፉ ሀገርን ማብቂያ ወደሌለው የጦርነትና የትርምስ አዙሪት ውስጥ ይከታታል።

ሰላምና መረጋጋት በሌለበት፣ የሕግ የበላይነት ባልተከበረበት ሀገር ውስጥ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስትመንት ሊኖር ስለማይችል ሕዝቡ ለከፋ ድህነት ይዳረጋል።

የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ማለት ልዩነቶችን በሃይል ሳይሆን በውይይት፣ በድርድርና በህግ አሰራር የመፍታት ጥበብ ነው። የፖለቲካ የስልጣን ምንጭ የሕዝብ ፍላጎት ብቻ ሲሆን ታላላቅ ሀገራዊ እሴቶች ይጎለብታሉ፡፡

የሀሳብ የበላይነት፣ ፓርቲዎችና መሪዎች ስልጣን የሚይዙት ሕዝብን በብረት አስፈራርተው ሳይሆን፣ በሚያቀርቡት አማራጭ የፖሊሲ ሀሳብና የልማት እቅድ ሕዝብን አሳምነው ይሆናል፤ በዚሁ አካሄድ የሀሳብ የበላይነትም ገዢ ሆኖ ይወጣል።

ሕዝብ የፈለገውን መሪ በነጻነት መርጦ ካስቀመጠ በኋላ፣ የስልጣን ዘመኑ ሲያልቅ በሰላማዊ መንገድና በምርጫ ካርድ ብቻ ስልጣኑን ለቀጣዩ አካል የሚያስተላልፍበት ሥርዓት ይገነባል። ይህ ለሀገር መረጋጋት ትልቁ ዋስትና ነው።

በሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ግለሰቦች ወይም ታጣቂዎች ሳይሆኑ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት እንደ ገለልተኛ ፍርድ ቤቶች፣ ነጻ የምርጫ ቦርድና የህግ አስከባሪ አካላት የበላይነት ይኖራቸዋል።

ይህንን እሴት በተግባር ለማዋል የሁሉም ወገን ቁርጠኝነትን ይጠይቃል።

በመጀመሪያ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎች ከ”እኔ ካልመራሁ ሀገር ትፍረስ” አባዜ ወጥተው የህዝብን ውሳኔ የመቀበል ስነ-ልቦና ሊኖራቸው ይገባል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ የዜጎች የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ማደግ ነው፤ ዜጎች መብታቸውንና ግዴታቸውን ለይተው በማወቅ በምርጫ ሂደት ላይ ልክ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ እንዳየነው ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በአጠቃላይ ጠብመንጃ ስልጣንን ሊያስጨብጥ ቢችልም ሰላምና ልማትን ግን ፈጽሞ ሊያመጣ አይችልም። የሀገር ህልውና፣ እድገትና አንድነት ሊረጋገጥ የሚችለው የሕዝብ ድምጽና ፍላጎት በነጻነት ሲከበር እና ልዩነቶች በሰለጠነ የውይይት ባህል መፈታት ሲችሉ ብቻ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.