ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ሥምምነት ከሶማሌ ላንድ ጋር ተፈራረመች
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ሥምምነት ከሶማሌ ላንድ ጋር ተፈራረመች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ታሪካዊ ነው የተባለውን የመግባቢያ ሠንድ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል፡፡
የኢፌዴሪ መንግሥት እና የሶማሌላንድ መንግሥት የፈረሙት የትብብር እና የአጋርነት መግባቢያ ሠነድ በተለያዩ ዘርፎች በቀጣይ ለሚኖራቸው ግንኙነቶች ማዕቀፍ እንደሚሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽኅፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
የመግባቢያ ሠነዱ የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ዕውን የሚያደርግ ፣ የባሕር በር አማራጮቿን የሚያሠፋ እንዲሁም የሁለቱን ወገኖች የፖለቲካ ፣ የዲፕሎማሲ ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናከር ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ሠነዱ ሀገራቱ በፖለቲካ እና በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሚኖራቸውን ግንኙነት የሚጎለብትበትን አካሄድ የሚያካትት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በሰጥቶ መቀበል መርኅ እና ሀገሪቷ ለጋራ ጥቅም ከጎረቤቶቿ ጋር የመሥራት ፍላጎት እና አቋሟን መልሶ የሚያጸና እንደሆነም ተመላክቷል፡፡
ሠነዱ ÷ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት እና ለአፍሪካ ቀንድ ትሥሥር የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑም ተጠቁሟል።
ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሠላም እና ደኅንነት የሚገባትን ሚና እንድትጫወት የተሻለ ዕድል እንደሚፈጥር ነው የተገለጸው፡፡