Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል መንግሥት የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ2 ሺህ ለሚልቁ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገና (ልደት) በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ2 ሺህ 741 ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ብርሃኑ ጎሽም እንዳሉት÷ የክልሉ መንግሥት የይቅርታ ቦርድ በአዋጁ መሠረት በክልሉ በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ ታራሚዎች ይቅርታ አድርጓል፡፡

በተሰጠው ይቅርታም 2 ሺህ 688 ወንዶች እና 53 ሴቶች ታራሚዎች የይቅርታው ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ከአሁን በፊት ይቅርታ ተደርጎላቸው ከ3 ዓመት ወዲህ ጥፋት የፈጸሙ አካላት ይቅርታቸውን በአግባቡ ባለመጠቀማቸው እንዲሠረዝ መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

ታራሚዎች የባሕሪ ለውጥ ሲያመጡ ይቅርታ ማድረግ የመንግሥት ሥራ መሆኑም አስታውቀዋል፡፡

ታራሚዎች ተስፋ እንዳይቆርጡ፤ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው መኖር እንደሚችሉ እና ተስፋ እንዳላቸው ለማሳየት ይቅርታው አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ይቅርታው በሕገ መንግሥት ይቅርታ የማይፈቀድላቸውን ታራሚዎች እንደማይመለከትም ነው ያሳወቁት፡፡

ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች የቅጣት መጠኑን በሚጠበቀው ልክ የፈጸሙ እንዲሁም በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የባህሪ ለውጥ ያመጡ ናቸው ማታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

በክልሉ የተጀመረው ሰላም ዘላቂ እንዲሆንም ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.