በመዲናዋ ከበዓላት ጋር በተያያዘ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለገና (ልደት) እና ጥምቀት በዓላት የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም በልዩ ትኩረት የተቀናጀ ስራ እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ እንደገለጹት÷ ከመጪዎቹ በዓላት ጋር በተያያዘ ጤናማ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር ለማስቻል በምክትል ከንቲባ የሚመራ ዐቢይ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
የአቅርቦት ችግር እንዳይኖር እና ወደ መዲናዋ በቂ ምርት እንዲገባም በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ዩኒየኖች እና የአርሶ አደር ማኅበራት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የምርት አቅርቦትና የገበያ ተደራሽነትን ከማስፋት አኳያም በተመረጡ ሰባት ቦታዎች ባዛሮች መዘጋጀታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎችም ሳምንቱን ሙሉ ግብይት እንዲፈፅሙ እየተደረገ ስለመሆኑ ገልጸው፤ ከነባሩ በተጨማሪ በአዳዲስ የገበያ ማዕከላትም በቂ ምርቶች እንዲቀርቡ መደረጉን አንስተዋል፡፡
በመደበኛ ገበያ ላይ የዋጋ ቁጥጥር ከማድረግ አንፃርም÷ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን እና ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ምርት የሚከማችባቸውን ቦታዎች በመለየት ድንገተኛ ፍተሻ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የበር ለበር ክትትልና ቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC(Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!