Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጠሉ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ ዓረቢያ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ያካተተ የኢትዮጵያ ልዑክ በሳዑዲ ዓረቢያ  የሥራ ጉብኝት አድርጓል።

ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ  የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሳዑዲ ዓረቢያው ልዑል  አልጋ ወራሽ  መሃመድ ቢን ሳልማን የላኩትን መልዕክት ለሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስረክበዋል።

በዚህ ወቅትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሳዑዲ ዓረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፈርሃን ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

በውይይቱ አቶ ተመስገን  ኢትዮጵያ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር በኢኮኖሚ፣በጸጥታ እና በሰው ሃይል ሥምሪት ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እየሠራች መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ የጋራ ኮሚሽን ሥብሰባ ማካሄድ፣ በሂደት ላይ ያለውን የሞያተኛ የሥራ ሥምሪት ስምምነት መፈራረም እና  በንግድ እና ኢንቨስትመንት መስክ ያለውን ትብብር ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሕጋዊ የባሕር በር ጥያቄ  በቀጣናው ለሚካሄደው የምጣኔ ሃብት ውህደት  የሚኖረውን ጠቀሜታ በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል።

ልዑል ፋይሰል ቢን ፈርሃን በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ  በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሳል አመራር እያስመዘገበችው ያለውን እድገት አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ  ለሳዑዲ- አፍሪካ ግንኙነት ድልድይ እና ወሳኝ ሀገር ነች ያሉት ልዑል ፋይሰል ቢን ፈርሃን ÷የሁለቱ ሀገራት  በሁሉም መስክ መተባበር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች በወቅታዊ የቀጣናው ሰላም እና ደኀንነት ሀሳብ በመለዋወጥ በአካባቢው ሰላም እና ደኀንነት እንዲሰፍን   ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ማንሳታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.