Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ሸኔን መርዳት ሙከራ ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የሸኔ ቡድንን መርዳት ሙከራ ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ።

ሴና ደበላ እና ሌንጮ አማኑኤል በ1996 ዓ.ም የወጣውን ህግ አንቀጽ 27/1/፤ 32 /1/ ሀ፤ ለ እና የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣዉን አዋጅ ቁጥር 1176/ 12 አንቀጽ 9 /2/ እና አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 31 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ሥር የተደነገገውን መተላለፋቸው ተነስቷል፡፡

በዚህም በሽብርተኛ ድርጅት መርዳት ሙከራ ወንጀል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ችሎት ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆናቸው በምዕራብ ኦሮሚያ ለሚንቀሳቀሰው ለሸኔ ሽብር ቡድን የሚውል ብዛታቸው 200 ወታደራዊ አልባሳት የአንዱን የዋጋ ግምት በ1 ሺህ ብር ለመግዛት በሸገር ከተማ ሰበታ ከተማ አስተዳደር ልዩ ቦታው ስታዲየም አካባቢ ተስማምተው በመጋቢት 17 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ሰዓት ሲሆን አዲስ ከተማ አስተዳደር አዲስ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው አውቶቡስ ተራ አካባቢ ከግብረ-አበሮቻቸው ጋር በማሰናዳት 90 ሺህ ብር ከፍለው ደንብ ልብሱን ሊቀበሉ ሲሉ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የፍትህ ሚኒስቴር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል የዓቃቤ ሕግ ክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው ችሎት ተከሳሾቹ ሽብርተኛ ድርጅት መርዳት ሙከራ ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ሲል የጥፋተኝነት ብይን መስጠቱን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ችሎቱ የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈባቸው፥ በሕግ አግባብ ተከሳሾቹ ከአድራጎታቸው ይታረማሉ፤ ሌሎች መሰል የወንጀል ተግባር እንዳይፈጽሙ ያስጠነቅቃል በማለት እያንዳንዳቸው በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ30 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.