ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሞሮኮ ወታደራዊ ልዑክ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሞሮኮ ምክትል ኢንስፔክተር ጀኔራል ስታፍ ሜጄር ጄኔራል አዚዝ ኢድሪሲ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት ልዩ ልዩ ወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ÷ከዚህ በፊት በሁለቱ ሀገራት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት መኖሩን እና በተለያዩ ጉዳዮች ምክንያት ተቋርጦ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡
አሁን የተዘጋውን በር ከፍተን አዲስ የግንኙነት መስመር ለመዘርጋት ውይይት እና ጉብኝት ማድረጉ መልካም ነገር ነውና እጅግ ደስተኞች ነን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሜ/ጄ አዚዝ እድሪሲ በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበርም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ ግዳጁን በብቃት መወጣት የሚችል ጠንካራ ወታደር ያላት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ወታደራዊ ትብብር ማድረግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ በማመን ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን አንስተዋል፡፡
የዛሬው ውይይት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት በአዲስ መልክ ለማደስ እንደሚበጅም ነው የገለጹት፡፡
በተጨማሪም በሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ተቀራርቦ በጋር ለመስራት በር እንደሚከፍት ጠቁመው÷በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ልዑካን ቡድን በሞሮኮ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን÷ በሚቀጥሉት ተከተታይ ቀናት የሞሮኮው ወታደራዊ ልዑክ በተቋሙ የተለያዩ ክፍሎች በመዘዋወር ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋል፡፡
ከጉብኝቱ በኋላ የሚደረገው የሃሳብ ልውውጥ እና ውይይት ቀጣይ በሁለቱ ሀገራት መካካል ለሚደረገው ወታደራዊ ስምምነት እና የአፍሪካዊ ወንድማማችነት መንፈስ ታላቅ መሰረት እንደሚጥል መጠቀሱንም የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡