ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ስምምነት ከኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ጋር ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱ በቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ በሚያካሄደው የግብርና ናሙና ቆጠራ ላይ የሚሰማሩ ባለሙያዎችን በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሰራተኞች ለምቶ ወደ ሥራ የገባውን የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓትን በመጠቀም ለመቅጠር የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል÷የሥታስቲክስ አገልግሎቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚያካሄደው የግብርና ናሙና ቆጠራ ባለፉት ዓመታት በገጠርና በከተማ ግብርና እንዲሁም በሌማት ትሩፋት የተሠሩ ሥራዎች ያስገኙትን ውጤት በትክክል ለመለካት የሚያስችል በመሆኑ ለሀገር በቀል ሪፎርም ሥራችን ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡
ከ22 ዓመታት በኋላ በሚሰበሰበውበዚህ ሥራ መረጃውን የሚያሰባስቡ ዜጎች ምልመላና ቅጥር በሚኒስቴሩ ሠራተኞች ለምቶ ወደ ሥራ በገባው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት አማካኝነት እንዲፈፀም ለማስቻል ስምምነቱ መደረጉን አንስተዋል፡፡
ይህም ፍትሃዊ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ የቅጥር ሒደቱን በማጠናቀቅ በፍጥነት ሥራውን ለማስጀመር እንደሚያስችል ነው የገለጹት፡፡
በኢትዮጵያውያን ወጣቶች የለማው የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት የሥራ ገበያውን ማዘመን፣ገበያው የሚፈልገውን የክህሎት አይነት መለየትና በርካታ የሥራ ዕድሎችን ለዜጎች በፍትሃዊነት የመፍጠር ዓላማ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት በመላ ሀገሪቱ የሚተገበርና መረጃዎችን በአጭር ጊዜና በጥራት ለማሰባሰብ እንደሚያስችል ጠቅሰዋል፡፡
ይህም የሥታስቲክስ አገልግሎቱ ለሚያካሄደው የግብርና ናሙና ቆጠራ በላቀ ደረጃ ተመራጭ እንዳደረገው መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡
በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ወጣቶች በየአካባቢያቸው በሚገኙ የሥራ ዕድል ጽ/ቤት በመገኘት የባዮሜትሪክ መረጃቸውን በመስጠት መመዝገብና በሥራው ላይ መሰማራት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡