Fana: At a Speed of Life!

በኢነርጂ ፍጆታ እና በልዩ ልዩ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ ተግባራዊ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ200 ኪሎ ዋት ሠዓት በላይ በሚጠቀሙ ደንበኞች የፍጆታ ሂሳብ ላይ እና አዲስ ደንበኛ ማገናኘትን ጨምሮ ደንበኞች በሚፈፅሟቸው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ክፍያዎች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተግባራዊ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የሚሆነውን የመኖሪያ ቤት የኤሌክትሪክ ኃይልና የውኃ ፍጆታ መጠን ለመወሰን ባወጣው አዋጅ ቁጥር 1341/2016) መመሪያ እና አዋጁን ለማስፈፀም በወጣው መመሪያ ቁጥር 1021/2016 መሠረት ክፍያው ከመስከረም ወር ጀምሮ ከ200 ኪሎ ዋት ሠዓት በላይ የተጠቀሙ ደንበኞች ላይ ተግባራዊ መደረጉን ነው አገልግሎቱ ያስታወቀው፡፡

በመመሪያው መሰረትም ከአገልግሎታችን ተጠቃሚ ደንበኞች ከወርሀዊ የፍጆታ ሂሳብ ጋር ተጨምሮ እንዲከፍሉ በማድረግ የተሰበሰበው ገንዘብ በየወሩ ለገቢዎች ሚኒስቴር ገቢ እንደሚያደርግም ነው የገለጸው፡፡

በዚህ መሠረት ደንበኞች ወርሃዊ የፍጆታ ሂሳብ በሚከፍሉበት ወቅት የፍጆታ መጠናቸው ከ200 ኪሎ ዋት ሠዓት በላይ ከሆነ እላፊ የመጣው የፍጆታ መጠን የተጨማሪ እሴት ታክስ ተሰልቶ ሂሳባቸው ላይ የሚደመር ይሆናል ተብሏል፡፡

ተቋሙ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተግባራዊ ያደረገው ከሕዳር ወር የክፍያ ደረሰኝ ጀምሮ ሲሆን÷ የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች ከመስከረም ወር ጀምሮ ያለባቸውን የኋላ ክፍያ በታሕሣሥ ወር በሚወጣው ቢል ላይ ተጨምሮ የሚከፍሉ ይሆናል ነው የተባለው፡፡

በተመሳሳይ የቅድመ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞችም ከመስከረም ወር ጀምሮ ባላቸው የፍጆታ መጠን መሠረት የኋላ ክፍያ በቀጣይ ይከፍላሉ መባሉን አገልግሎቱ ለፋና ዲጂታል አረጋግጧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደንበኞች ለአገልግሎቱ በሚከፍሉት ልዩ ልዩ ክፍያዎች ላይም ተግባራዊ እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቲቪ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 1278/2015 ዓ.ም በተሰጠው ስልጣን መሰረት ዓመታዊ የቴሌቪዥን አገልግሎት ክፍያ የሚሰበስብ መሆኑን አገልግሎቱ አስታውሷል፡፡

ይህን ወርሃዊ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ ስርዓትን በመጠቀም በየወሩ እንዲሰበስብ ሕዳር 2 ቀን 2015 ዓ.ም በተፈረመ የሁለቱ ተቋማት ስምምነት መሠረት አገልግሎቱ የቴሌቭዥን አገልግሎት ክፍያ በወርሐዊ በደንበኞች የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳብ ላይ በመጨመር እንዲከፍሉ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሷል፡፡

በዚህም ወርሐዊ የኤሌክትሪክ የፍጆታ መጠናቸው ከ50 ኪሎ ዋት ሠዓት በላይ የሆኑ ደንበኞች 10 ብር ከወርሐዊ ኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳብ ጋር የቴሌቪዥን አገልግሎት ክፍያ እየከፈሉ ነው ተብሏል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.