አዲስ አበባ ለአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ስኬታማነት ያላት ትጋት ይደነቃል- ሱዳናዊ ጋዜጠኛ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔን በስኬት ለማስተናገድ እያደረገች ያለው ዝግጅት የሚደነቅ መሆኑን ሱዳናዊው የፕሬስ ፀሐፊ፣ ተንታኝ እና የሚዲያ አማካሪ መኪ ኢልሞግራቢ ገለፀ፡፡
ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ የሕብረቱን ጉባዔ ሲከታተል መቆየቱን አውስቶ÷ ኢትዮጵያ ስብሰባው በምቹ ሁኔታ ውስጥ ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ ሁሌም የምታደርገውን ትጋት አድንቋል፡፡
ከጉባዔው ጋር በተያያዘም ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች እና ለሕብረቱ መሪዎች የቪዛ ሂደት በኦንላይን መሰጠቱ ቀልጣፋ እና የወረቀት ሥራን ያስቀረ መሆኑን በመጥቀስ ሂደቱ እንዳስደነቀው ጠቅሷል፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንግድ የኦንላይን የመዳረሻ ቪዛ መሰጠቱም በአኅጉሪቱ ሕዝቦች መካከል ያልተቋረጠ ግንኙነት እንዲፈጠር ያስችላል ብሏል፡፡
ኒውዮርክ፣ ዋሽንግተን እና ጄኔቫን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ዓለም አቀፋዊ ጉባዔዎች መከታተሉን ጠቅሶ÷ በአዲስ አበባም ከእነዚህ ከተሞች ጋር የሚስተካከል የእንግዳ ተቀባይነት ባህል መኖሩን አንስቷል፡፡
መዲናዋ በሕብረቱ ጉባዔዎች ለእንግዶች እያደረገች ያለው እንክብካቤ እና የምታዘጋጃቸው ባሕላዊ ትርዒቶች በሕብረቱ አባል ሀገራት መካከል የወንድማማችነት መንፈስ እንዲፈጠር የሚያደርጉ መሆናቸውን አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ለጠንካራ የአፍሪካ አንድነት እና ትብብር መጎልበት ሁሌም የምታደርገው ጥረት እንደሚደነቅም ነው የገለጸው፡፡
የፊታችን የካቲት 17 እና 18 ለሚካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ አዲስ አበባ ዘርፈ-ብዙ ዝግጅቶችን እያደረገች ነው፡፡
በወንደሰን አረጋኸኝ እና ሚኪያስ አየለ