Fana: At a Speed of Life!

ብልጽግና ፓርቲ የተከተለው አካሄድ የጸረ ሰላም ቡድኖችን ዓላማና ሕልውና ማክሸፍ አስችሏል – አቶ ይርጋ ሲሳይ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ የተከተለው በመርሕ ላይ የተመሰረተ አካሄድ የጸረ ሰላም ቡድኖችን ዓላማና ሕልውና ለማክሸፍ አስችሏል ሲሉ በፓርቲው የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ ገለጹ፡፡

አቶ ይርጋ እንዳሉት÷ የለውጡ አመራር የሚከተላቸው ሀገራዊ አንድነትን ማዕከል ያደረጉ፣ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት እና ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ልማትን እውን የማድረግ መርሆዎች ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሁሉም ማዕዘናት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ያለው ቁርጠኛ አቋም ፍሬዎች መታየት መጀመራቸው የፓርቲውን እሳቤዎችና ሀገራዊ ራዕይ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ማስቻሉን አንስተዋል፡፡

የፓርቲው ጥረት በአማራ ክልል ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገቡን ጠቁመው÷ የክልሉን ሰላምና የሕዝቡን ደህንነት ለአደጋ አጋልጠው የቆዩትን ፀረ-ሰላም ቡድኖች እውነተኛ ማንነትና ዓላማ ሕዝብ እንዲገነዘብ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በአሁኑ ወቅት ፀረ-ሰላም ቡድኖቹ በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክመው ወደማይቀረው የክስመት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ነው ያመላከቱት፡፡

ፓርቲው ከምሥረታው ጀምሮ ዘላቂ ሰላምን እውን ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው አጀንዳዉ አድርጎ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

የማህበረሰብ ውይይትን በስፋት በማካሄድ፣ ከታሪክ የተወረሱ ሀገራዊ የትርክት ቅራኔዎችን ለመፍታት በመስራትና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማምጣት የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል፡፡

በተጨመሪም ሁሉን አቀፍ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሲሰራ መቆየቱን ነው ያብራሩት፡፡

በሌላ በኩል በአማራ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩና አካባቢውን ለማተራመስ ሲጥሩ በነበሩ ፀረ-ሰላም ቡድኖች በርካታ ፈተናዎችን ሲያስተናግድ መቆየቱን ጠቁመው÷ በፓርቲውና በሕዝቡ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክልሉ አስደናቂ ለውጦችን እውን ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በመከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራልና የክልል መንግስታትና የፀጥታ ሃይሎች የተቀናጀ ጥረትም የፀረ-ሰላም ቡድኖች ተጽእኖ በእጅጉ መቀነሱን አንስተዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ችግሩን ለመፍታት መሰረታዊ የማህበረሰብ ተሳትፎን በማበረታታቱና በሕዝብ ባለቤትነት በሚመራ ስልት ላይ ትኩረት በማድረጉ የፅንፈኛ ቡድኖችን አጀንዳዎችና ዓላማ በማክሸፍ ዜጎች በጋራ ሆነው በሰላም ዙሪያ እንዲሰባሰቡ በማድረግ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቅሰዋል።

የተሻሻለው የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ማህበራዊ ልማትን እያበረታታ እንደሚገኝ መናገራቸውንም የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.