ለቅርሶች ጥገና የሚውል ኖራ የሚያመርት ፋብሪካ ለመገንባት ዝግጅት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ለታሪካዊ ቅርሶች ጥገና ግብዓት የሚውል ኖራ የሚያመርት ፋብሪካ ለመገንባት የሚያስችል ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ኃላፊ መልካሙ ፀጋዬ እንዳሉት፤ ለታሪካዊ ቅርሶች ጥገና ግብዓት የሚያመርት የኖራ ፋብሪካ ባለመኖሩ በቅርሶች ጥገና ላይ ችግሮች ሲስተዋሉ ቆይተዋል፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍ ጥናት ሲካሄድ መቆየቱን አስረድተው፤ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የኖራ ፋብሪካ ለመገንባት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡
ፋብሪካው ከዚህ ቀደም ለቅርሶች ጥገና ይወጣ የነበረውን እስከ 100 ሚሊየን ብር የሚደርስ ዓመታዊ ወጭ እንደሚያስቀርም ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
በቀን እስከ 300 ኩንታል ኖራ የማምረት አቅም እንደሚኖረው ጠቁመው፤ ይህም ቅርሶችን በተያዘላቸው ጊዜ ጠግኖ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
በበላይነህ ዘላለም