ኢንቨስት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመት ፎረም እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ እና ነገ በአዲስ አበባ የሚካሄደው “ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2025” ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም መካሄድ ጀምሯል።
በፎረሙ መክፈቻ ላይ ፕሬዘዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የልማት አጋሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢንቨስትመንት ፎረሙ በመንግስት ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ እና የልማት አጋሮች የጋራ ትብብር የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል።
ፎረሙ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጭ ማስተዋወቅ እና የኢኮኖሚ እድገትን ማሳለጥ ላይ እንዳተኮረ ተመላክቷል።
በፎረሙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተለወጠ በመጣው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስነ ምህዳር ዙሪያ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ ተያይዞም የመንግስት እና የግል አጋርነት ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ምክክር እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።