በቀጣይ የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች የዲጂታል ክኅሎትን መሠረት እንደሚያደርጉ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣይ የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎችም ሆኑ ሌሎች ጥቅሞች የዲጂታል ክኅሎትን መሠረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አመላከተ፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ወሳኝ ከሆኑ መሠረቶች የዲጂታል ክኅሎት መገንባት እና ክኅሎቱን በዲጂታል ሥነ-ምኅዳሩ ውስጥ በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሥራዎች በዲጂታል ላይ እየተመሠረቱ፣ በኢንተርኔት አማካኝነትም በአንድ ስፍራ ባለመወሰን አዲስ ዕድል እየሰጡ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
በዚህ አዲስ ዕድል መጠቀም የሚችሉት ተፈላጊ የሆኑ የዲጂታል ክኅሎት ያላቸው ብቻ መሆናቸውን ገልጸው፤ ወጣቶች ይህን በመገንዘብ መንግሥት ባመቻቸው የኢትዮ ኮደሮች ስልጠና እንዲጠቀሙ መክረዋል፡፡
በዓመቱ ከተያዘው ዕቅድ አንጻር አሁን ያለው የሰልጣኝ ቁጥር ጥሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ካላት የወጣት ቁጥር እና ዕድሉን አሟጥጦ ከመጠቀም አንጻር አሁንም ጠንክረን መሥራት እና ብዙ ወጣቶች ዕድሉን እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ወጣቶች ስልጠናውን በተገቢው መንገድ እንዲወስዱም በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው