ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመራጭ የኢንሹራንስ ገበያ ለመሆን እየሰራች ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመራጭ የኢንሹራንስ ገበያ ለመሆን እየሰራች መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
51ኛው የአፍሪካ ኢንሹራንስ ተቋም ዓመታዊ ኮንፈረንስ እና አጠቃላይ ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ÷ በኢትዮጵያ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ በመደረጉ ኢኮኖሚው መዘመን መቻሉን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ በተሻለ እድገት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው÷ ለፈጠራ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ፣ ንግድን የሚያሳድግ እና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በግብርና፣ በአምራች እና በቱሪዝም ዘርፎች ማሳካት የሚቻለውን ደረጃ ሁሉ ለመድረስ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
የኢንሹራንስ ዘርፉን የፋይናንስ ዘርፍ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለአብነትም ገለልተኛ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡
ባለስልጣኑ ፈጠራን የሚያሳድግ፣ ውጤታማ ቁጥጥርን የሚያጠናክር እና በዋናነት የፖሊሲ አስፈጻሚዎችን የሚከላከል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይህም በቤት ልማት፣ በመሰረተ ልማት እና በሪል ስቴት ዘርፍ አዳዲስ የፋይናንስ እና የኢንሹራንስ ዘርፎች ተሳትፎን ሊያሳድግ የሚችል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ኢንቨስተሮች ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ጊዜው አሁን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ መንግሥት የኢንሹራንስ ዘርፉን እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል፡፡
ኮንፈረንሱ የክፍያ ሚዛንን ማስተካከል፣ የአፍሪካ የእዳ ጫና እና የሀገራት እዳ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ እንዴት ተጽዕኖ ያሳድራል? በሚል መሪ ሐሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በለይኩን ዓለም