Fana: At a Speed of Life!

የጤና ባለሙያዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በሒደት ለመፍታት በትኩረት ይሰራል – አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የጤና ባለሙያዎች የውይይት መድረክ ”የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር ዕድገት” በሚል መሪ ሃሳብ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በክልሉ የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል በዘርፉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።

የጤናው ዘርፍ ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀጣይ እድገት ታሳቢ ተደርጎ እየተከናወነ ሲሆን÷ ለዚህም አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን በርካታ መዋዕለ ንዋይ እየፈሰሰ ነው ብለዋል።

በተለይም የሕክምና ተቋማትን በፍትሃዊነት ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የሕክምና መሳሪያዎችን በማሟላት ረገድ መንግስት ሰፊ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የጤና ባለሙያዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመቋቋም እስከ ሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ሕዘብን በማገልገል የአርበኝነት ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።

የጤና ባለሙያዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አቅምን መሰረት በማድረግ በጊዜ ሒደት የሚፈቱ መሆናቸውን አንስተው÷ባለሙያዎቹ በገቡት ቃለ መሃላ መሰረት ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ተላብሰው መስራት እንደሚገባቸውም አብራርተዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ በበኩላቸው÷ በክልሉ ለችግሮች የማይበገር የጤና ሥርዓትን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከለውጡ ወዲህ በተሰሩ ሥራዎች የእናቶችና ህፃናትን ጤና በማሻሻል እንዲሁም የተላላፊ በሽታዎችን ሥርጭት በመቀነስ ረገድ ውጤታማ ሥራዎች እንደተከናወኑ መግለጸቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የጤና ሥርዓቱን በማዘመን፣ ዘላቂ የጤና ፋይናንስ ሥርዓትን በመገንባትና ክልሉን የሜዲካል ቱሪዝም በማድረግ ረገድም ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.