በገጠር አካባቢዎች ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የዋሉ መጽሐፍት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መደመር፣ የመደመር መንገድ፣ የመደመር ትውልድ እና የመደመር መንግሥት መጽሐፍትን ለንባብ አብቅተዋል፡፡
ከመጽሐፍት ሽያጩ የተገኘውን ገቢም ለበጎ አድራጎት ሥራዎች አውለዋል።
ይህ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልት ከመደበኛው የመንግሥት በጀት ውጪ ጥራት ያለውን ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ የፋይናንስ ምንጭ ሆኗል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያው መደመር መጽሐፍ ሽያጭ የተገኘው ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ለቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ተበርክቷል።
ጽህፈት ቤቱ ይህንን ገቢ በመጠቀም ቀደም ሲል ጥራት ያለው የትምህርት መሠረተ ልማት ባልደረሰባቸው የሀገሪቱ የገጠርና ሩቅ አካባቢዎች በርካታ ዘመናዊ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል።
በመጽሐፍ ሽያጭ ገቢ የተገነቡት ትምህርት ቤቶች ከመደበኛ የገጠር ትምህርት ቤቶች በተሻለ መልኩ ዘመናዊ መገልገያዎችን ያካተቱ ናቸው፡፡
ትምህርት ቤቶቹ የተሟላ የሳይንስ ቤተ ሙከራ፣ የኮምፒውተር ክፍሎች እና ሰፊ የንባብ ማዕከላት አሏቸው።
ለአስተማሪዎችና ለተማሪዎች ምቹ የሆኑ ሰፊ የመማሪያ ክፍሎችና አዳራሾችን አካትተው የተገነቡ ናቸው።
ግንባታዎቹ የተከናወኑት ቀደም ሲል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባልነበረባቸው፣ ተማሪዎች ረጅም ርቀት ተጉዘው ለመማር በሚገደዱባቸው የሀገሪቱ የገጠርና ሩቅ ወረዳዎች ላይ ነው።
የገጠር ተማሪዎች በተለይም ሴቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለመማር ረጅም ርቀት ወደ ከተማ የመጓዝ እና ትምህርት የመቋረጥ ችግራቸውን ቀርፏል።
በአፋር፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ እና ሌሎችም ክልሎች ከ30 በላይ ዘመናዊ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።
አንድ መሪ የራሳቸውን የአእምሮ ውጤት በመሸጥ የትውልድ መገንቢያ የሆነውን የትምህርት ዘርፍ መደገፋቸው በሀገሪቱ የበጎ አድራጎት ባህልን አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
መንግሥት ለሌሎች አንገብጋቢ ዘርፎች የሚመድበውን በጀት ሳይነካ፣ በትምህርት ጥራት ላይ ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር አስችሏል።
ይህ በመጽሐፍት ሽያጭ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት በጎነት፣ ዕውቀትን በዕውቀት የመገንባት እና የመደመርን እሳቤ በተግባር የመተርጎም ትልቅ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።