Fana: At a Speed of Life!

የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር አዋጅ ጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር አዋጅ የተረጅነት አስተሳሰብን በመሻገር የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ሁነኛ መሳሪያ ነው አሉ።

ምክር ቤቱ በ34ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር አዋጅን አፅድቋል፡፡

በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር)፥ የአዋጁን የዝግጅት ሂደትን አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

የአደጋ ሥጋት አመራር የውሳኔ ሃሳብ አዋጁ ከተረጅነት አስተሳሰብ በመላቀቅ ለአደጋ ሥጋት በሀገር አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚረዳ ጠንካራ ሃሳብ የያዘ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም አዋጁ ያልተማከለ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ሥርዓት በመዘርጋት በየደረጃው የሚገኙ የፌደራልና የክልል መንግስታት ተግባርና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡበትን ድንጋጌ እንደያዘ ገልጸዋል።

የአደጋ ሥጋት ቅበላ ሥራዎችን ከዘላቂ የልማት ዕቅዶችና መርሃ ግብሮች ጋር በማስተሳሰር የሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ አሰጣጥ መርሆችን የተከተለ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ከአደጋ በፊት፤ በአደጋ ጊዜና በድህረ አደጋ ወቅት የቅድመ መከላከልና መልሶ ማቋቋም ተግባራትን በውጤታማነት ማከናወን የሚያስችል አደረጃጀት እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

በአዋጁ የዝግጅት ሂደት የፌደራል ስርዓትን ከሚከተሉ ዘጠኝ ሀገራት ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ የተሻለ ግብዓት የታከለበት መሆኑን በማስረዳት የምክር ቤቱ አዋጁን እንዲያጸድቀው የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል።

የምክር ቤቱ አባላት፥ አዋጁ ተረጅነትን በመሻገር የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ሁነኛ መሳሪያ በመሆን ያገለግላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አዋጁ ከተረጂነትና ከጠባቂነት አስተሳሰብ የሚያላቅቅ፣ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ የሚያስችልና ነባር የመረዳዳት እሴትን የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸዋል።

ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎችን በሀገር አቅም ለመደገፍ ከደመወዝተኛው ላይ በየወሩ ገንዘብ ለመሰብሰብ ተቀምጦ የነበረው አንቀጽ እንዲሰረዝ መደረጉንም በበጎ አንስተዋል።

በቀጣይ ከህብረተሰቡ የሚሰበሰቡ ገቢዎች ሕግ፣ ደንብ እና መመሪያን በተከተለ አግባብ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳሰበው ምክር ቤቱ፤ የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር አዋጅን በቁጥር 1386/2017 በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.