በ2017 እንደ ሀገር ታላላቅ ድሎች ተመዝግበዋል – አቶ ፍቃዱ ተሰማ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 2017 በጀት ዓመት እንደ ሀገር ታላላቅ ድሎች የተመዘገቡበት ነው አሉ የብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ፡፡
የ2017 በጀት ዓመት የአፈጻጸም ግምገማና የ2018 ዕቅድ ላይ ያተኮረ መድረክ “ጠንካራ አደረጃጀት ለሁለንታዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ዕለት በጎንደር ከተማ ተጀምሯል፡፡
አቶ ፍቃዱ ተሰማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በ2017 ዓ.ም እንደ ሀገር በርካታ ድሎችና ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ የተሠሩ ስራዎች፣ የኮሪደር ልማት እና ሠላምን ለማጽናት የተከናወኑ ተግባራት አንጸባራቂ ውጤት ተገኝቶባቸዋል ብለዋል፡፡
የተገኙ ውጤቶችን መሰረት በማድረግም የኑሮ ውድነትና የህዝብን የመልማት ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ የበለጠ መስራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ካጋጠመው የጸጥታ ችግር በመውጣት በክልሉ የተሟላ ሰላምና ብልጽግና ለማረጋገጥ የአደረጃጀቶችን አቅም ማጎልበትና መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ጠቅሰው፥ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ መንገዶች እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በበላይነህ ዘለዓለም