Fana: At a Speed of Life!

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 90 ሺህ ዩኒት ደም ለማሰባሰብ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ደም እና ኅብረ-ኅዋስ ባንክ አገልግሎት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 90 ሺህ ዩኒት ደም ለማሰባሰብ እየተሰራ ነው አለ።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክረምት ወራት በደም እጥረት ምክንያት የሰዎች ህይወት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሥራ እየተሰራ ይገኛል።

በዚህም የደም ልገሳ መርሐ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ በተጀመረው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል በመሆን ሕብረተሰቡ ደም መለገስ እንዲችል ንቅናቄ ተጀምሯል ብለዋል።

በዚህም ብሔራዊ የወጣቶች ደም ልገሳ ማህበር አስተባባሪነት ከሐምሌ 1 ቀን 2017 እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 90 ሺህ ዩኒት ደም ለማሰባሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።

ከአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 40 ሺህ ዩኒት ደም ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የማህበረሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ጽሕፈት ቤቶችን ጨምሮ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የደም ልገሳን በእቅዳቸው አስገብተው በክረምት መርሐ ግብሩ ደም ለመለገስ እና ለማስለገስ እየሰሩ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡

የሚተካን ደም በመለገስ የማይተካን ህይወት መታደግ ትልቅ ስጦታ በመሆኑ የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች ደም በመለገስ ህይወት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአድማሱ አራጋው

 

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.