ክልሉን የልማትና የብልጽግና ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ – አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን የልማትና የብልጽግና ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጥላሁን ከበደ፡፡
የክልሉ ምክር ቤት 5ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት የታዩ ችግሮችን በማረም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣በከተማና መሠረተ ልማት እና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች ስኬት ተመዝግቧል።
ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠልም የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር የሚሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በመሆኑም ያደሩ የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ቁርጠኝት መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በምክር ቤቱ በመጀመሪያ ቀን ውሎ የክልሉ የ2017 በጀት አመት የዕቅድ አፈፃፀም ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን በቀረበው ሪፖርት ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።
የጉባኤው የመጀመሪያ ውሎ ማጠናቀቂያ ላይ አቶ ጥላሁን ከበደ፣ የምክር ቤቱ አባላትና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በአርባምንጭ ከተማ ጫኖ ሚሌ ቀበሌ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል።
በማስተዋል አሰፋ