አጓጊው የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ …
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2025/26 የውድድር ዓመት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ምሽት የአምናው የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል ከቦርንማውዝ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል፡፡
የ2024/25 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በሊቨርፑል አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ለወራት ቡድናቸውን ሲያጠናክሩ ቢቆዩም አሁንም እያጠናከሩ ይገኛሉ፡፡
እንደ ቼልሲ እና ማንቼስተር ሲቲ አይነት ክለቦች ደግሞ ከሊጉ መጠናቀቅ በኋላ በክለቦች ዓለም ዋንጫ ውድድር የተሳተፉ ሲሆን÷ ቼልሲ በፍጻሜው ፒኤስጂን በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳቱ የሚታወስ ነው፡፡
የፕሪሚር ሊጉ ክለቦች ባለፈው ዓመት የነበረባቸውን የቡድን ክፍተት ለመሙላት በርካታ ሚሊየን ፓውንድ በማውጣት በዝውውር መስኮቱ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ታላላቆቹ ሊቨርፑል፣ ቼልሲ፣ አርሰናል እና ሁለቱ የማንቼስተር ከተማ ክለቦች በዝውውር መስኮቱ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙ ክለቦች ናቸው፡፡
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በክረምቱ የዝውውር መስኮት እስካሁን ድረስ ጀርሚ ፍሪምፖንግ፣ ሚሎዝ ኬርኬዝ፣ ጆርጂ ማማርዲያሻቪሊ እና ፍሎሪያን ዊርትዝን አስፈርሟል፡፡
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ሊያም ዴላፕ፣ ኢስቴቫኦ ዊሊያን፣ ጄሚ ጊተንስ፣ ዮሬል ሀቶ፣ ዦአዎ ፔድሮ የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡
ባለፉት ተከታታይ ሶስት ዓመታት በሊጉ 2ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አርሰናል ቪክተር ዮኬሬሽ፣ ኖኒ ማዱኬ፣ ክርስቲያን ኖርጋርድ፣ ክርስቲያን ሞስኬራ እና ማርቲን ዙቢሜንዲን በማስፈረም ይበልጥ ቡድኑን አጠናክሮ ለአዲሱ የውድድር ዘመን ቀርቧል፡፡
በ2024/25 የውድድር ዓመት ደካማ የውድድር ዘመን ያሳለፈው ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ÷ ማቲያስ ኩና፣ ዲዮጎ ሊዮን፣ ብሪያን ምቤሞን እና ቤንጃሚን ሼሽኮን በማስፈረም ቡድኑን የማጠናከር ስራ ሰርቷል፡፡
ወደ ሊጉ የተመለሰው ሰንደርላንድ በዝውውር መስኮቱ በንቃት ከተሳተፉ የሊጉ ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን÷ ግራኒት ዣካን ጨምሮ ሰባት ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡
ከወራት በኋላ ዛሬ ምሽት የሚመለሰው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አዲሱ የውድድር ዓመት ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ሮድ ስታዲየም ቦርንማውዝን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጀመራል፡፡
የመጀመሪያ የመክፈቻ ጨዋታውን ከአምናው ሻምፒዮን ሊቨርፑል ጋር የሚያደርገው ቦርንማውዝ ግብ ጠባቂውን ኬፓ አሪዛባላጋን ጨምሮ ተከላካዮቹን ሚሎስ ኬርኬዝ፣ ዲን ሁይሰን እና ዛባርኒን ለሌሎች ክለቦች አሳልፎ ሰጥቷል፡፡
የፊታችን እሁድ ማንቼሰተር ዩናይትድ ከአርሰናል በኦልድትራፎርድ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ጨዋታ ነው፡፡
የዘ አትሌቲክ ፀሐፊዎች የ2025/26 የውድድር ዓመት የሊጉን ዋንጫ የአምና የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በድጋሚ እንደሚያነሳ ግምታቸውን ያስቀመጡ ሲሆን÷ አርሰናል፣ ማንቼስተር ሲቲ እና ቼልሲ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቅቃሉ ሲሉም አመላክተዋል፡፡
በ2024/25 15ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ በዚህኛው የውድድር ዘመን 8ኛ ደረጃን ይዞ ይጨርሳል በማለት የዘ አትሌቲክ ፀሐፊዎች ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook WMCC
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!