5ኛው የፋና ላምሮት የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ነገም ቀጥሎ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ደማቁ እና አጓጊው 5ኛው የፋና ላምሮት የአሸናፊዎች አሸናፊ የድምፃውያን ውድድር በነገው ዕለትም ቀጥሎ ይካሄዳል።
ባለፈው ሳምንት በአንድ የተገናኙት የሁለቱ ምድብ ተወዳዳሪዎች ሰባት ሆነው የፍፃሜ መዳረሻ ውድድራቸውን ነገ ሲያካሂዱ፤ ኤፍሬም ጌታቸው፣ ናሆም ነጋሽ፣ ጴጥሮስ ማስረሻ፣ ካሳሁን ዘውዱ፣ እየሩሳሌም አሰፋ፣ ማዕረግ ሀይሉ እና እዮቤል ፀጋዬ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ።
በቀጥታ ስርጭት በሚካሄደው ውድድር ተወዳዳሪዎች በተመልካቾች በተመረጡላቸው ሙዚቃዎች ጭምር ይፎካከራሉ።
የዕለት አቀራረብ ላይ መሰረት በሚያደርገው በፋና ላምሮት ውድድር ላይ በዳኞች እና በተመልካቾች ድምፅ በየሳምንቱ አንድ ተሰናባች ይኖራል።
ነገም እንደተለመደው አንድ ተጋባዥ ድምፃዊ በክብር እንግድነት ይገኛል።
ውድድሩ በፋና ቴሌቪዥን እና በሁሉም የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች በቀጥታ ስርጭት ይተላለፋል።
በ13ኛው ሳምንት አራት ምርጥ ተወዳዳሪዎችን ይዞ የፍፃሜ ውድድሩን የሚያካሂደው ፋና ላምሮት የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ከ3 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ሽልማት የተዘጋጀለት ሲሆን፤ የዋናጫ እና የአዲስ ሙዚቃ ሽልማትንም ያበረክታል።
በለምለም ዮሐንስ