Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሩዝ ሰብል ልማትን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ በክልሉ የሩዝ ሰብል ልማትን በማሳደግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው አለ።
የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ኸሊፋ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ በ2017/18 ምርት ዘመን 13 ሺህ 144 ሄክታር መሬት በሩዝ ሰብል ለመሸፈን ታቅዶ 7 ሺህ 636 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል።
በክልሉ መተከል ዞን የተጀመረውን የሩዝ ሰብል ልማት ኢኒሼቲቭ ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘንድሮ በአሶሳ ዞን ሶስት ወረዳዎች ላይ 300 ሄክታር መሬት በሩዝ መሸፈኑን ገልጸዋል።
በሙከራ ደረጃ የተዘራው የሩዝ ሰብል ቁመና ተስፋ ሰጪ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው ፤ በሄክታር እስከ 32 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት የሩዝ ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ ዘር ከማቅረብ ጀምሮ በሩዝ ሰብል ልማት ለተሰማሩ አርሶ አደሮች የተለያየ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
በ2018 ዓ.ም የበጋ ወቅት የሩዝ ሰብልን በመስኖ ለማልማት ዕቅድ ተይዟል ያሉት አቶ ባበክር ኸሊፋ፤ የመስኖ መሰረተ ልማት እና ሌሎች ግብዓቶችን ከወዲሁ ለማሟላት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.